” ከግብ ጠባቂው በስተቀር ተጫዋች ስንመለምል ለአንድ ሚና ብለን አናመጣም” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ

በአዲሱ የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የተጫዋቾች አጠቃቀም ነው።

ከቅድመ ውድድር ጊዜ ጀምሮ ተጫዋቾቻቸውን በሌሎች ጊዜያት ሲጫወቱባቸው ከነበሩ ሚናዎች በተቃራኒ የተለያዩ ቦታዎች በማሰለፍ የሚገኙት አሰልጣኙ ከዚህ ቀደምም በሌሎች ክለቦች ቆይታቸው ተመሳሳይ ውሳኔዎች ቢወስኑም በዚህ የውድድር ዘመን ግን ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል።

አሰልጣኙ ቡድናቸው በዕለተ ቅዳሜ ስሑል ሽረን ከረታበት ጨዋታ በኋላ በጉዳዩ ዙርያ ያላቸውን ሃሳብ እንደሚከተለው ሰጥተዋል።

“ተጫዋች ስንመለምል ለአንድ ቦታ ብለን አናመጣም። ጋዜጠኛም ሌላም ሰው ድሮ የሚያቀውን ነገር ሊጠብቅ ይችላል፤ እሱ ያለ ነገር ነው። በኛ ግምት ግን ከግብ ጠባቂው በስተቀር አንድ ተጫዋች ስናመጣ አሰልጣኙ ትምህርት ይሰጥና እሱ ነው ቦታውን የሚወስነው። በተፈጥሮ ለአንድ ተጫዋች እዚህ ነው ቦታህ ተብሎ የተወሰነ ነገር የለም። ብዙ ያመጣናቸው ተጫዋቾች ቢያንስ ከሁለት በላይ በሆኑ ቦታዎች ላይ መጫወትን አስለምደናል። ታዳጊዎቹ እነ ሰመረ ሃፍታይ እና ስምዖን ማሩም በተከላካይ ቦታ መጫወት አስተምረናል፤ ስለዚህ ሁሉም ይህን መማር አለባቸው። ተጫዋች አንድ ቦታ ላይ ብቻ ስታስረውና አንድ ቦታ ብቻ ስታጫውተው እግርኳስ በስነ-ስርዓት ሊገባው አይችልም። ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ