በሠፈር በሚደረግ ውድድር በመጫወት ላይ ሳለ በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የአርባአምስት ደቂቃ ምልከታ ብቻ የተስፋ ቡድኖች ውስጥ ሳይጫወት በቀጥታ በ2009 ለከፍተኛ ሊጉ ክለብ ወልቂጤ ከተማ በመጫወት እስከ 2010 ቆይታን ያደረገ ሲሆን በክለቡ ቆይታውም በሁለቱም ዓመት በድምሩ አስራ አምስት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ወልቂጤን በመልቀቅ ወደ ሀዋሳ ሲመጡ ተጫዋቹ አብሮ ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡ ብሩክ አምና በጉዳት በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ከሜዳ ቢርቅም በመስመር እና አጥቂነት ተሰልፎ በመጫወት ሦስት ግቦችን አግብቶ አጠናቋል፡፡
ወጣቱ የመስመር እና የፊት አጥቂ በአዳማ ከተማ ዋንጫ የጀመረው አስደናቂ አቋሙ በፕሪምየር ሊጉም ቀጥሎ ሀዋሳ ከተማ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነ ኳስን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ ተጫዋቹ በክለቡ እያሳየ ስላለው አስደናቂ ብቃት እና ወቅታዊ አቋሙ እንዲሁም ስለእግርኳስ አጀማመሩ በማንሳት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የእግርኳስ አጀማመርህ እና ወደ ክለብ የተቀላቀልክባቸው ጊዜያት ምን ይመስሉ ነበር ?
“በፕሮጀክት እግር ኳስን ስጀምር ተመስገን ዳና ጋር በ13 ዓመት ቡድን ውስጥ በመጫወት ነበር። ከተመስገን ቡድን በኋላ ህይወት ብርሀን ወደሚባል የሠፈር ቡድን ውስጥ ነው የሄድኩት። አሰልጣኝ ተመስገን ጋር ስሰራ ቦታው ይርቀኝ ስለነበር ህይወት ብርሀን ደግሞ አቅራቢያዬ ስለነበረ ነው ያ የሆነው። በዚህ ቡድን መጫወቴ ለኔ ጠቅሞኛል በተለይ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ቡድኔን ወክዬ አርባምንጭ ላይ መጫወቴ ልምድ እንድይዝ በሚገባ ረድቶኛል ፤ ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ። ወደ ክለብ የገባሁት ደግሞ በክረምት ስብስብ ቡድን ውስጥ ሆኜ በአጋጣሚ የሀዋሳ ተስፋ ቡድን ውስጥ ልያዝ በነበረበት ወቅት አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ አይቶኝ ነው። በሠፈር ውድድር ላይ ስጫወት አርባ አምስት ደቂቃ ብቻ አይቶኝ ‘እንሂድ’ አለኝ። ከፍተኛ ሊግ አዲሴ ሲያሰለጥን ወደ ነበረው ወልቂጤም ወሰደኝ፡፡”
በተስፋ ቡድኖች ተጫውተህ ሳታልፍ ነው በቀጥታ ወደ ክለብ የገባኸው ፤ በመጀመሪያ ክለብህ ወልቂጤ የነበረህ ቆይታ እንዴት ነበር ?
“የወልቂጤ ቆይታዬ አሪፍ ነበር። ጥሩ እንድሆን የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳም አስተዋጽኦ አለበት። አዲስ እንዳልሆን እና ፍርሀት በውስጤ እንዳይኖር ይመክረኝ ነበር፡፡ ‘ዋናው መስራትህ ብቻ ነው የሚፈለገው ያን ካደረክ ስራህም ላይ ትኩረት ካደረክ ጥሩ ነገር ይኖርሀል’ እያለ ስለመከረኝ በተወሰነ መልኩ ብደናገርም በሂደት ግን አልተቸገርኩም ፤ ማግባት ጀመርኩ፡፡
ወደ ሀዋሳ ከተማ አምና ስትመጣ የሙከራ ጊዜ ተሰጥቶህ ነበር የፈረምከው። ያን ጊዜ እና የክለቡ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታህ እንዴት ነበር ?
“አምና በሀዋሳ ከተማ ደስ በሚል ሁኔታ አሳልፌያለሁ ፤ ትንሽ ግን ይከብድ ነበር ጉዳትም ነበረብኝ። ከአምናው ዘንድሮ ግን የተሻለ ነገር ለማሳየት በሚገባ ሰርቻለሁ ያን ለማድረግ ደግሞ እየጣርኩ ነው፡፡ ለኔ ሀዋሳ ከተማ መጫወትን አልመው ነበር፡፡ ይሄን ዕድል አሰልጣኝ አዲሴ ሲሰጠኝ እኔም በሚገባ ተጠቅሜያለሁ፡፡”
በሦስት የሊግ ጨዋታዎች ለሀዋሳ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ተፅህኖህ ከፍ እያለ መጥቷል። ከአምናው ምን የተለየ ነገር ሰርተህ ነው አቅምህን ያሳደከው ? በቀጣይስ ምን እንጠብቅ ?
“አምና የነበረብኝን ስህተት ለመቅረፍ በደንብ ሰርቻለሁ። ምክንያቱም የተሻለ ቦታ መጫወትም ሆነ ማደግን እፈልጋለሁ፡፡ ለዛም በርትቼ እየሰራሁ ነው፡፡ በገባሁበትም አጋጣሚ ግብ እያገባሁ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ማሳደግ እፈልጋለሁ፡፡ ካለፈው ዓመት በተሻለ በምገባባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ቡድኔን ጠቅሜ መውጣት እፈልጋለሁ፡፡ ክለቤም አምና ከነበረው የበለጠ ውጤት እንዲኖረው እና እንዲሻሽል እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ቡድን ሁላችንም ለዚህ ዓላማ በወኔ እየሰራን ነው፡፡ አሁን የአሸናፊነት መንፈስ ላይ ነው ያለነው እግዚአብሔር ካለ የተሻለ ነገር በዚሁ እናሳካለን፡፡ በግል ደግሞ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ጠንክሬ መገኘት አለብኝ፡፡ ከሀገር ውጪ መጫወትም እፈልጋለሁ፡፡ ለሀገሬ ተመርጬ እንደሌሎቹ ተጫዋቾች ለመጫወትም አልማለው።”
ወደ ኳሱ ዓለም ለመግባት አርዓያ ወይም መነሻ የሆነህ ተጫዋች ማነው ?
“ለኔ መነሻዬ ጌታነህ ከበደ ነው። እሱን አርአያ እያደረኩ ነው ያደኩት፡፡ ልጅ እያለው ጌቴነህ ደቡብ ፖሊስ ሲጫወት አየው ነበር፡፡ ያኔ የሱ አድናቂ ነበርኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ሜዳ እየገባሁም ጨዋታዎቹን አይ ነበር፡፡ እሱን አይቼ እዚህ ላይ ደርሻለሁ፡፡
ምስጋናህ እንደዲደርሳቸው የምትፈልጋቸው ሰዎች ካሉ?
“በቅድሚያ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ ፤ በመቀጠል ያሰለጠኑኝን በሙሉ አመሰግናለሁ። ተመስገን ዳናን በተለይ ደግሞ አምኖኝ እዚህ እንድደርስ ያደረገኝ አዲሴ ካሳን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በተጨማሪም አሰልጣኝ ሙላት ማቲዮስንም አመሰግናለሁ። ”
© ሶከር ኢትዮጵያ