ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ጌዴኦ ዲላ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች የጀመረው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ ሲቀጥል ከሜዳው ውጪ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ጌዴኦ ዲላ 3-0 በማሸነፍ ዓመቱ የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም 10:00 ላይ የተጀመረው ጨዋታው በፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን የጎል ሙከራ ለማስተናገድም ጊዜ አልፈጀበትም። በ2ኛው ደቂቃ አምበሏ እታገኝ ሰይፉ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ጎል የላከችው ኳስ ለጥቂት የወጣው ሙከራ አዲስ አበባን ቀዳሚ ለማድረግ በእጅጉ የቀረበ ነበር።

በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉት ዲላዎች አመዛኙ ጊዜያቸውን በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ቢያሳልፉም በፊህ መስመር ስልነት ጎድሏቸው ታይቷል። በ22ኛው ደቂቃ ትዝታ ፈጠነ ጥሩ አጋጣሚ አግኝታ ግብ ጠባቂዋን ለማለፍ ስትሞክር የተያዘባት እና በ34ኛው ደቂቃ ድንቅነሽ በቀለ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ መትታ የጎሉ ቋሚ የመለሰባትም ተጠቃሽ መጀመርያ አጋማሽ የዲላ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ዲላዎች ተሻሽለው በመግባት አጋጣሚዎችን ወደ ጎል የመቀየር አቅማቸውንም አሳድገው የቀረቡ ሲሆን ከ10 ደቂቃ በኋላም የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። ድንቅነሽ በቀለ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ስታወጣው ከሳጥን ውጪ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ረድኤት አስረሳኸኝ በግሩም ሁኔታ አክርራ በመምታት ድንቅ ጎል ማስቆጠር ችላለች።

ከጎሉ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የዲላዎቹ ተከላካዮች ቤተልሄም አስረሳኸኝ እና ፋሲካ በቀለ ኳስ ለማራቅ ድንገት በፈጠሩት ግጭት ቤተልሄም ደረቷ ከባድ ጉዳት አስተናግዳለች። ሆኖም በቦታው የአምቡላንስም ሆነ የቃሬዛ አገልግሎት ባለመኖሩ በቡድኑ ወጌሻ እና ተጫዋቾች ርብርብ ከሜዳ የወጣች ሲሆን ለተሻለ ህክምናሞ ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች። በመጀመርያው ሳምንትም የአምቡላንስ እና በቂ የሕክምና እርዳታ ሰጪዎች አለመኖራቸውን መጥቀሳችን የሚታወስ ሲሆን የዛሬው ክስተትም ለአወዳዳሪው አካል የማንቂያ ደውል ሆኖ አልፏል።

ለደቂቃዎች የተቋረጠው ጨዋታ ቀጥሎ ዲላዎች የመጀመርያውን ጎል ባስቆጠሩበት መንገድ ለማስቆጠር ሙከራዎች አድርገዋል። በዚህም አማካይዋ ስመኝ ምህረት በ74ኛው ደቂቃ ከርቀት አክርራ የመታችው ኳስ የአአ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ገነት አንተነህ የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ወደ ጎልነት ተቀይሯል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይራ የገባችው ነፃነት ሰውአገኝ በተመሳሳይ ከርቀት የመታችው ኳስ የጎሉን ቋሚ ለትሞ ሲወጣ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ ነፃነት ሳጥን ውስጥ ያገኘችውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ሦስተኛውን ጎል አስቆጥራለች።

ከጎሉ በኋላ ዲላዎች በመልሶ ማጥቃት መልካም አጋጣሚዎች ቢያገኙም በቀላሉ ሲያመክኑት ተስተውሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በዲላ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ዲላ ከሁለት ጨዋታ 4 ነጥብ ሲሰበስብ አዲስ አበባ ከተማ ሁለቱንም ጨዋታዎች በተመሳሳይ 3-0 ተሸንፎ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ