በሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ሳምንት አራፊ የነበረው መቐለ 70 እንደርታ በታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ከመከላከያ ጋር አድርጎ 2-1 አሸንፏል።
በመከላከያዎች ብልጫ የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ጥሩ ፉክክር የታየበት እና በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርካታ ሙከራዎች የታየበት ነበር። በመቐለዎች በኩል ሳምራዊት ኃይሉ በሁለት አጋጣሚዎች ከቅጣት ምት የሞከረቻቸው ኳሶች እና ዮርዳኖስ ምዑዝ ያደረገችው ሙከራ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ሲሆኑ በእንግዳዎቹ መከላከያዎች በኩልም አይዳ ዑስማን ያደረገችው ሙከራ እና መዲና አወል በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት አክርራ መታ ፍረወይኒ ገብሩ እንደምንም ያዳነቻቸው ሙከራዎች በጦሮቹ በኩል የታዩ ወርቃማ ዕድሎች ናቸው።
በሃያኛው ደቂቃ መቐለዎች በዮርዳኖስ ምዑዝ አማካኝነት መሪ ሆነዋል፤ አጥቂዋ ግብ ጠባቂዋ የተፋችውን ኳስ አግኝታ ነበር ያስቆጠረችው።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ነበር ግብ የታየበት። በአርባ ስምንተኛው ደቂቃም አስካለ ገ/ፃድቅ ከርቀት አክርራ ግሩም ግብ በማስቆጠር የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች። መቐለዎች ከግቧ በኋላም ተቀይራ በገባችው ሳሮን ሰመረ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል።
መከላከያዎችም በሃምሳ ሶስተኛው ደቂቃ በመሰሉ አበራ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ማጥበብ ችለዋል። መከላከያዎች ከግቡ በኋላም በመዲና ዐወል የረጅም ርቀት ሙከራ አቻ ለመሆን ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በመቐለ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በውጤቱ መሠረት ዘንድሮ ወደ ሊጉ ያደጉት መቐለዎች በፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያው ድላቸውን አስመዝግበዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ