ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በቅርቡ የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርጉ ነው

የሁለቱን ሀገራት ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠንከር በማሰብ በቅርቡ ሁለቱ ሀገራት በአስመራ ከተማ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርጉ እንደሆነ ታውቋል።

ከዚህ ቀደም ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የሁለቱን ሀገራት ወንድማማችነት ለማጠናከር በማሰብ አስመራ ከተማ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ በሁለቱም ሀገራት መካከል ስምነት ቢደረግም በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ታሪካዊ ጨዋታ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል።

በቅርቡ የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነት ለማጠንከር በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት የሚመራ የሀገራችን የባህል ቡድን አስመራ መግባቱ ይታወቃል። የዚህ አካል የሆነው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ በቅርቡ እንደሚደረግ የኤርትራ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ አብርሃ ለሴካፋ ስብሰባ ወደ ዩጋንዳ ከማቅናታቸው አስቀድሞ አዲስ አበባ ከተማ ለአንድ ቀን በነበራቸው ቆይታ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

” የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን በአሁን ወቅት በሴካፋ ዋንጫ እየተሳተፈ ይገኛል። ለፍፃሜ ዋንጫም መድረሱ ይታወቃል። ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ሁኔታዎችን አመቻችተን በቅርብ በሚባል ጊዜ አስመራ ከተማ ላይ ጨዋታው እንዲደረግ ከስምምነት ደርሰናል።” ብለዋል።

በ1990 በተቀሰቀሰው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኑ ከኤርትራ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ አድርገው የማያውቁ ሲሆን አሁን በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ወደ ሠላም በመመለሱ ከ15 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአስመራ ውድድር አድርጎ መመለሱ ይታወቃል። ኢትዮጵያውያን ዳኞችም የአስመራው ውድድርን መምራታቸው የቅርብ ትውስታ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ