ፌዴሬሽኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር የገባው ውዝግብ በቅርቡ ዕልባት ያገኛል

በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አሸማጋይነት እየታየ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የተመልካች ገቢ አከፋፋልን በተመለከተ ከፌዴሬሽኑ ጋር የተፈጠሩት ውዝግብ በቅርቡ መፍትሔ ያገኛል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታድየም ከሚገባ ተመልካች ገቢ 32% ፌዴሬሽኑ ይከፍሉ እንደነበረ ይታወቃል። ይህ አሰራር በየትኛው ዓለም የሌለ መሆኑና ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ውጭ ያሉ 14ቱ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ይህን ገቢ ለፌዴሬሽኑ ሲፈፅሙ አለመቆየታቸው “እኛስ ለምን?” የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አስገድዷቸው ቆይቷል።

ከ2012 የውድድር ዘመን ጀምሮ የተመልካች መግቢያ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ ከአሞሌ ድርጅት ጋር በጋራ በመስራት የትኬት ሽያጩን በዳሽን ባንክ መሸጥ ገቢውን ክለቦቹ ብቻ መውሰድ ከጀመሩ ሁለተኛ ሳምንታቸው ላይ ይገኛሉ። ፌዴሬሽኑን ከ32% ላይ የምወስደውን ገቢ በስታድየሙ ለሚገኙ የተለያየ ተግባራትን ለሚያከናውኑ ሠራተኞች የምከፍለው ገቢ በመሆኑ ክለቦቹ ከእኔ እውቀና ውጭ ይህን ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም በማለት ቅሬታውን አቅርቧል።

ስታድየሙን በላይነት የሚያስተዳድረው እና ጉዳዮን በአሸማጋይነት የያዘው ኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ሁለቱ ክለቦች እና የፌዴሬሽኑ ተወካዮች በተገኙበት ከሰሞኑን ውይይት አድርገዋል። በመጨረሻም ኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ሁለቱ ክለቦች ያነሱት ጥያቄ ተገቢነት ያለው በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ሀሳባቸውን እንዲያከብር ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል። ሆኖም የፌዴሬሽኑ ተወካዮች ጉዳዩን ለሥራ አስፈፃሚ አባላት በማሳወቅ በቀጣይ የፌዴሬሽኑን አቋም ምን እንደሆነ እናሳውቃለን በማለት ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

ይህም ጉዳይ በቀጣይ ቀናት ዕልባት እንደሚሰጠው እየተጠበቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የተመልካች ገቢ ጥቅማቸውን እያስጠበቁ ይቀጥላሉ ማለት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ