ወልቂጤ ከተማ በ4ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሰበታ ከተማ ጋር ላለበት ጨዋታ የወልቂጤ ስታዲየም የማሻሻያ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ዝግጁ ቢሆንም የመጨረሻ የይሁንታ ፈቃድ እንዲያገኝ ከዐቢይ ኮሚቴው የተላኩ ግለሰቦች ሜዳውን በአካል ሳይመለከቱ ጨዋታው በተለዋጭ ሜዳ እንዲደረግ መወሰናቸው አግባብ ስላለመሆኑ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።
ዘንድሮ ሊጉን በአዲስ መልክ ተዋቅሮ እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐቢይ ኮሚቴ በቅድሚያ ባደረገው የተሳታፊ ክለቦች የሜዳ ግምገማ መሠረት ጨዋታ ለማካሄድ ብቁ አይደሉም ብሎ ከለያቸው ስታዲየሞች አንዱ የሆነው የወልቂጤ ስታዲየም ሲሆን በዚህም መሠረት ላለፉት ወራት ስታዲየሙ መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ሥራዎች ሲሰሩለት መቆየቱ ይታወሳል። በዚህም ወልቂጤ ከተማዎች የመጀመሪያ ሁለት በሜዳቸው ላይ ማድረግ የነበረባቸውን ጨዋታዎች በባቱ ሼር ሜዳ እንዲሁም በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
የማሻሻያ ስራዎቹ የተጠናቀቁለት የወልቂጤ ስታዲየም ለጨዋታ ዝግጁ ስለመሆኑ በሰፊው ሲገለፅ ቢቆይም እግዱን ባስተላለፈበት የሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ የማረጋገጫ ፍቃድ ለማግኘት በዚህ ሳምንት በሜዳው ተገኝተው የመስክ ምልከታ እንዲያደርጉ ሁለት የኮሚቴው አባላት ቢጠበቁም መገኘት አለመቻላቸውና በ4ኛ ሳምንት ከሰበታ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ በተለዋጭነት ባስያዙት አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም እንዲደረግ መወሰኑ ከመርህ ውጭ የተሰራ ስራ መሆኑ ቅሬታ ውስጥ እንደከተታቸው የወልቂጤ ከተማ ስፓርት ክለብ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ሰለሞን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
አቶ አበባው በንግግራቸው “መጀመሪያ በተደረገው የመስክ ምልከታ መሠረት ማሻሻል ይገባችኃል የተባልናቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በተባለው መልኩ አከናውነን የጨረስን መሆናችንን በደብዳቤ ለዐቢይ ኮሜቴው ያሳወቅን ሲሆን በባለፈቱ ቀን ደሞ በስልክ ስንጠይቅ ሜዳውን ለመልከት የተላኩ ሁለት የዓብይ ኮሚቴ አባላት እሮብ ዕለት የሚመጡ መሆኑን ተግልፆልናል። በዚህ ሳምንት መጥተው ያለውን ሁኔታ ተመልክተው እግዱ ይነሳል ብለን በተስፋ ብንጠብቅም መገኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ህዝባችን መልካም የሚባል ባህሪ ያለውና ጨዋታውን በሜዳው ለማከናወን ከፍተኛ ሥራ ሰርቶ እዚህ ያደረሰውን ሥራ መጥቶ አለማየት ቡድናችን በሜዳው በመጫወቱ ሊያገኛቸው የሚችሉ ጥቅሞችን እንዲያጣ ከወዲሁ ጫና እየተደረገብን እንደሆነ ነው እየተሰማን ያለው። በአካል መጥቶ መሆን እና አለመሆኑን መገለፅ ነበረበት። ” ብለዋል።
ጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ በመጪው ቅዳሜ እንዲደረግ መርሃግብር የወጣለት የወልቂጤ ከተማና የሰበታ ጨዋታ በየት ሜዳ እንደሚደረግ ማወቅ አልተቻለም። ሶከር ኢትዮጵያ የዐቢይ ኮሚቴውን ምላሽ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ጥረታችን ሰምሮ ምላሹን ሲሰጡን ይዘን የምንመለስ መሆኑም እናስውቃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ