ለሴቶች ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች አሰልጣኞች ተሾሙ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት እና ከ17 ዓመት በታች የሴት ብሄራዊ ቡድኖች ከቀጣዩ ወር ጀምሮ የዓለም ዋንጫ አካል የሆኑ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያከናውናሉ። ለዚህ ዝግጅትም የዋና እና ረዳት አሰልጣኞች ሹመት ተከናውኗል።

በቀጣዩ ወር ከቡሩንዲ ጋር የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ለሚያከናውነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ፍሬው ኃ/ገብርኤል ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል። ወጣቱ አሰልጣኝ በሴቶች እግርኳስ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ሲሆን በ2008 ደደቢትን ለፕሪምየር ሊግ ድል ማብቃት ችሏል። የሲዳማ ቡና ሴቶች ቡድን እና የከፍተኛ ሊጉ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን በአሰልጣኝነት የመራው ፍሬው ባለፈው ዓመት በሞሮኮ እና ስዊድን በተሰጡ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።

የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብሬኤል ምክትል በመሆን የተሾመችው ሕይወት አረፋይኔ ናት። የመቐለ 70 እንደርታን አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለች የምትገኘው ኢንተስራክተር ሕይወት ቡድኑን ወደ ዘንድሮው ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ማሳደግ ችላለች።

በዓለም ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ መጋቢት ወር ላይ ከጅቡቲ ጋር የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ለሚያደርገው ብሔራዊ ቡድን ሳሙኤል አበራ በዋና አሰልጣኝነት ተሹሟል። አዳማ ከተማን የ2011 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን እንዲሆን ያስቻለው ሳሙኤል ረዳት ሆና እንድትሰራ የተመረጠችው ደግሞ ሰርክአዲስ እውነቱ ናት። አሰልጣኟ ከዚህ ቀደም በ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት መሥራቷ ሚታወስ ሲሆን በቅርቡ የባሀር ዳር ከተማ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ሆና መሾሟ የሚታወስ ነው።

እንደ ፌዴሬሽኑ ገለፃ ከሆነ የአሰልጣኞቹ ምርጫ እና ምደባ የተከናወነው በእግር ኳስ ልማት ምክትል ጽ/ቤት ኃላፊ፣ በሴቶች እግር ኳስ ልማት እና ውድድር ቋሚ ኮሚቴ፣ የቴክኒክ እና ልማት ቋሚ ኮሚቴ እና በቴክኒክ ዳይሬክቶሬት የጋራ ሥራ ተካሂዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ