” ቦታዬን አጣለሁ ብዬ በፍፁም አልሰጋም” የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብጠባቂ ባህሩ ነጋሽ

ከክቡር ይድነቃቸው መታሰቢያ ውድድር ላይ በአጋጣሚ ተመልክተውት ነበር አሰልጣኞች ገና በታዳጊ ዕድሜው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ እንዲቀላቀል ያደረጉት። ብዙ ትዕግስት በሚጠይቅ ፈተና ውስጥ አልፎ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ለአራት ዓመታት በመጫወት ችሏል። በኋላም ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ያለ ምንም ጨዋታ ለሁለት ዓመታት ከቡድኑ ጋር እየሰራ ቆይቷል። በዘንድሮ የውድድር ዘመን እስካሁን ባለው የሊጉ ሦስተኛ ሳምንት ጉዞ ከአዳማ ከተማ ቀጥሎ ጎል ያልተቆጠረበት ቅዱስ ጊዮርጊስን በግብጠባቂነት እያገለገለ ይገኛል። ፈረሰኞቹ የአአ ከተማ ዋንጫን በአሸናፊነት ሲያጠናቅቁም በሁሉም ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ለድሉ ትልቁን አስተዋፆኦ ተወጥቷል። ባህሩ ነጋሽ!

ባህሩ ስለ ግብጠባቂነት ህይወቱ እና ሌሎች ነገሮች እንዲያወራን የዛሬ የሶከር ኢትዮጵያ እንግዳ አድርገነዋል። መልካም ቆይታ

ትውልድ እና ዕድገትህ የት ነው?

ተወልጄ ያደግኹት ወደ አስኮ መንገድ በተለምዶ አጠራሩ ብርጭቆ ፋብሪካ በሚባል ሰፈር ነው። ለቤተሰቦቼ ሦስተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነኝ። እንደማንኛውም ልጅ በሠፈር ውስጥ እየተጫወትኩ ነው ያደኩት። በኋላ ነው ወደ ፕሮጀክት አምርቼ ልምምድ መስራት፣ መጫወት የጀመርኩት።

ከቤተሰብህ በዚህ ስፖርት ያለፈ ይኖር ይሆን?

(እየሳቀ…) ኧረ በፍፁም! የመጀመርያም የመጨረሻ እኔ ነኝ። ማናቸውም በእግርኳሱ አልፈው አያቁም።

ታዲያ እንዴት ወደ ግብጠባቂነቱ ልታመራ ቻልክ?

ግብጠባቂ የመሆን ፍላጎት ኖሮኝ አይደለም ወደ ስፖርቱ የገባሁት። መጀመርያ ሰፈር ውስጥ ታላላቆቼ ሲጫወቱ በማየት በእግሬ ኳስ እጫወት ነበር። እንደ አጋጣሚ ግብጠባቂ ሲጎላቸው ከሁሉም ታናሽ ልጅም ስለነበርኩ እንደ ቀልድ ግብጠባቂ አድርገውኝ ገባሁኝ ። በመቀጠል የሆነ የሠፈር ውድድር ነበር፤ በዛው ግብጠባቂ ሆኜ ቀረሁ። አንድ ጓደኛዬ ጥሩ ነገር እንዳለኝ አውቆ አስኮ ፕሮጀክት እንድገባ አድርጎኝ በዛው ቀጥያለው።

በአስኮ ፕሮጀክት የነበረህ ቆይታ ምን ይመስል ነበር?

ይገርምሀል የሆነ ወቅት ግብጠባቂነትን ትቼው ነበር። ያው እንደምታቀው እኛ ሀገር ግብጠባቂ መሆን አሰልቺ እና አስቸጋሪ ነው። ብዙ ግብጠባቂ ሆነህ እንድትጫወት የሚያደርጉ የተመቻቹ ዕድሎች የሉም። የምትወድቅበት ሜዳ በራሱ ምን ያህል ለጉዳት እንደሚያጋልጥ ይታወቃል። ለስድስት ወር በቃ አልሰራም ብዬ ትቼው ነው በድጋሚ የተመለስኩት ።

ታዲያ እንዴት ተመልሰህ መጫወት ጀመርክ?

በቃ በድጋሚ መጫወት እንዳለብኝ ጓደኞቼ ሲገፋፉኝ ተመልሼ በ2005 በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ውድድር ላይ መጫወት ጀመርኩ። በወቅቱም የማደርገው እንቅስቃሴ መልካም የሚባል እና ተስፋ የሚጣልብኝ መሆኑን አውቀው ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ (ድሬ) አማካኝነት ጥሪ ቀርቦልኝ መጫወት ችያለው። በመቀጠል ነው ከ2006 ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን መቀላቀል የቻልኩት።

በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ለአራት ተከታታይ ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድኖች መጫወት ችለሀል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የነበረህን ቆይታን እንዴት ታስታውሰዋለህ?

ለግብጠባቂነት ህይወቴ ትልቁን መሠረት የጣልኩበት ጊዜ ነው። እንደምታቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከእኔ በፊት እጅግ በርካታ ስመ ጥር በረኞችን ከታችኛው ቡድን በማሳደግ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ እንዲጫወቱ ማድረግ ችሏል። እኔም ይሄን አውቅ ስለነበር በጣም ነበር ጠንክሬ እሰራ የነበረው። በተለይ ሮበርት ኦዶንካራን እያየሁ ማደጌ በጣም ጠቅሞኛል። ከእርሱ ብዙ ነገር ተምሬያለው። እናም በታዳጊ ቡድን ውስጥ የነበረኝ ቆይታ ጥሩ ነበር።

ወደ ዋናው ቡድን መቼ ማደግ ጀመርክ ?

2009 በቢጫ ቲሴራ ነው ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የጀመርኩት። በዚሁ ዓመት ከ20 ዓመት ቡድኑ እየተመላለስኩ መጫወት ቀጥዬ 2010 ነው ወደ ዋናው ቡድን ሙሉ ለሙሉ ማደግ የቻልኩት።

በዋና ቡድን የነበረህ የሁለት ዓመት ቆይታህ ምን ይመስል ነበር?

ጥሩም ከባድም የሚባል ነበር። ጥሩነቱ ለእኔ ወደ ፊት በትልቅ ደረጃ ለመጫወት እና ሀገሬን ለማገልገል ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያክል ቡድን ውስጥ አድጎ መጫወት በራሱ የሚሰጥህ ትልቅ ደስታ እና ተነሳሽነት አለ። ከዚህ ባለፈ እንደሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የሚያስመጣቸው ግብጠባቂዎች በጣም ትልቅ ሥም ያላቸው በመሆናቸው ለእኔ በጣም ጠቅሞኛል፤ ብዙ ተምሬበታለው። ከባዱ ነገር ደግሞ ለአንድ ግብጠባቂ ጥሩ ሆኖ ለመውጣት ተደጋጋሚ ጨዋታ ያስፈልገዋል። እኔ ደግሞ ከልምምድ ውጭ ለሁለት ዓመት ተጫውቼ አለማወቄ ከባድ ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ ግብጠባቂ መሆን ትዕግስት ይፈልጋል። እንተ ደግሞ ያለፉትን ዓመታት ወደ ዋናው ቡድን ብታድግም የመጫወት ዕድል አለማግኘትህ ፈታኝ እንደሚሆንብህ አስባለሁ። ትዕግስትን በሚፈታተነው በዚህ የግብጠባቂነት ህይወትህ ውስጥ ውጣ ውረዱን እንዴት ታየዋለህ?

በጣም ትዕግስት ይፈልጋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ከመሆኑ አንፃር የሚያስመጣቸው ግብጠባቂዎች በጣም ጥራት ያላቸው ከመሆናቸው አኳያ ከእነርሱ ጋር ተፎካክሮ የመሰለፍ እድል ለማግኘት በጣም ትዕግስት ይፈልጋል፣ ይከብዳልም። እንድያውም አንዳንድ ሰዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንድወጣ ወደ ሌላ ክለብ እንዳመራ ይመክሩኝ ነበር። ሂድና ሌላ ቦታ ተጫወት እያሉ ይነግሩኝ ነበር። ይገርምሀል ግን ሁልጊዜም ምንተስኖት አዳነ ይነግረኝ ነበር። ‘የትም መሄድ የለብህም ማሸነፍ ከቻልክ እዚህ ቤት ነው። ተፎካክረህ ማሸነፍ ያለብህ ማንነትህንም ማሳየት ያለብህ እዚህ ቤት ነው።’ እያለ በተደጋጋሚ ይነግረኝ ነበር። ይህው ፈጣሪ ይመስገን አሁን በአጋጣሚ ዕድሎችን አግኝቼ እየተጫወትኩ እገኛለሁ።

እንዳልከው የኬኒያዊው ግብጠባቂ ማታሲ እና የለዓለም ለረዥም ጊዜ መጎዳት ለአንተ የመጫወት ዕድል ይዞልህ መጥቷል። በአአ ከተማ ዋንጫ ሙሉ ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደግሞ እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችመጫወት ችለሀል። እስኪ ዕድሉን ካገኘህ በኋላ ያለውን ሁኔታ እና ስለ ወቅታዊ አቋምህ አጫውተኝ?

ከሲቲ ካፑ ልጀምርልህ። ያው ቅድም እንደነገርኩህ ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ካደኩ በኃላ ለሁለት ዓመት ምንም ዓይነት ጨዋታ አድርጌ አላውቅም። ግብጠባቂ ደግሞ እንደምታቀው ከጨዋታ ሲርቅ ከታይሚንግ አጠባበቅ ስህተቶች እና ሌሎች ነገሮች ይኖራሉ። በዚህ ሲቲ ካፕ ላይ እንዴት? ምን ማድረግ አለብኝ በማለት የአዕምሮ ስራ ስሰራ ቆይቻለው። እውነት ለመናገር ላዕለም ብዙ ነገር ይመክረኝ ነበር። ወደ ሜዳ ስገባ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ይነግረኝ ነበር። የመጀመርያ ጨዋታ ላይ የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩብኝ። ሆኖም ከጨዋታ ጨዋታ ራሴን እያሻሻልኩ በሲቲ ካፑ ላይ ሦስት ጎል ብቻ ነው የተቆጠረብኝ። ውድድሩም ብዙ ነገሮችን አስተምሮኝ አልፏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የግብጠባቂ አሰልጣኛችን ንዲዜዬ ኤሚ በክፍተቴ ላይ ትኩረት በማድረግ እያሰራኝ እንዳሻሽል እያደረገኝ ነበር። በፕሪምየር ሊጉ ላይ እስካሁን በሦስት ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድል አግኝቼ ጎል ሳይቆጠርብኝ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለሁ። ከዚህ በላይም ክለቤን ማገልገል እፈልጋለው።

በሊጉ እስካሁን በሦስት ጨዋታ ከአዳማ ከተማው ጃኮ ፔንዜ ጋር በጋራ ጎል አልተቆጠረብህም…

አዎ ጥሩ ጅማሮ ነው እያደረግኩ ያለሁት። ይህ ደግሞ የእኔ ብቻ ሳይሆን አብረውኝ የሚጫወቱ የቡድን አጋሮቼ እገዛ ነው። በቀጣይ ከዚህ በላይም ቁጥሩን ከፍ እያደረግኩ መሄድ እፈልጋለው።

አጋጣሚዎች ናቸው ወደ ቋሚ አሰላለፍ እንድትገባ ያደረገህ። ምን አልባት አንደኛ እና ሁለተኛ ግብጠባቂዎች ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ጨዋታ ሲመለሱ የአንተ የመጫወት ነገር ስጋት ውስጥ ይገባል። አሁን ከምታሳየው እንቅስቃሴ እንፃር ወደ ፊት የመሰለፍ ዕድል አጣለው ብለህ ትሰጋለህ ?

በፍፁም አልሰጋም፤ አሁን እያሰብኩ ያለሁት አሳዳጊ ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስን በማስፈልገው ሰዓት ማገልገል ነው። ምንም የምሰጋው ነገር የለም። ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ደግሞ ሰርተህ ደክመህ የራስህን ብቃት ማሳየት ከቻልክ ይህን ዕድል እነጠቃለው ብዬ አላስብም። እርግጥ ነው ግብጠባቂ ላይ አንድ ሰው ነው ተመራጭ የሚሆነው። አንተ የተሻልክ ከሆነክ አቅምህን ማሳየት ከቻልክ የማትመረጥበት ምንም ምክንያት የለም። በአጠቃላይ ግን እኔ መናገር የምፈልገው ስለ ነገ አያሳስበኝም አሁኑ ሙሉ ትኩረቴ ክለቤን ማገልገል ባለብኝ ሰዓት ማገልገሌ እና ራሴን እያሻሻልኩ ለተሻለ ዕድል መሄድ እንጂ ስለነገ ማሰብ አልፈልግም።

ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እየተጫወትክ አድገሀል። አሁን ያለህበት ደረጃ ለመድረስህ ምሳሌ የምታደርገው ሰው አለ?

እንደሚታወቀው ያደኩት ሮበርት ኦዶንካራን እያየው ነው። በዚህም በጣም ዕድለኛ ነኝ ከዚህ ትልቅ ግብጠባቂ ጋር አብሮ መስራት በመቻሌ። ለእኔ ትልቁ መነሻዬ እርሱ ነው። እሱን መሆን እየተመኘው ነው ያደኩት። በመቀጠል ታዳጊዎች ላይ መስራት የሚወደው እና እኔ ትኩረት በማድረግ ድክመቴን እየነገር እንዳሻሽል ጥሩ ልምምዶችን እየሰጠ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ትልቁን ሚና የተወጣው የግብጠባቂ አሰልጣኛችን ኤሚ ነው። ከዚህ ባለፈ በሀሳብ፣ በምክር በአዕምሮ ጠንካራ አድርጎ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ያደረገኝ ምንተስኖት አዳነ ነው። ሁሉንም ከልብ ማመስገን እፈልጋለው።

ሮበርትን ካነሳህ በአአ ከተማ ዋንጫ ላይ በብዛት እንዲሁም በፕሪምየር ሊጉ አንድ ጨዋታ ላይ እንደተመለከትኩህ ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጭ ያለው እንቅስቃሴህ ከሮበርት ጋር የመመሳሰል ነገር ይታይብሀል። ኳስ አያያዝህ ሁሉ ሳይቀር እርሱን ነው የምትመስለው…

(እየሳቀ…) አዎ ልክ ነህ! ያው ቅድም ነግሬሀለው፤ እርሱን እያየሁ፣ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እየተመለከትኩ ነው ያደኩት። አሰልጣኛችንም የሚያሰራን አንድ ዓይነት በመሆኑ ያ ይመስለኛል ወደ እርሱ እንቅስቃሴ ልሳብ የቻልኩት።

በቀጣይ ምን ታስባለህ ስለ ክለብህ? ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወትን?

ግልፅ ነው። እንደማንኛውም ተጫዋች ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለው። ከሀገሬ ጋር ብዙ ደረጃ መድረስ እፈልጋለው። በተለይ ከክለቤ ጋር በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የተለየ ታሪክ መስራት እፈልጋለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ