በቤኒሻንጉል ክልል እና በስደተኞች ጣቢያ የአሰልጣኞች ሙያ ማሻሻያ ኮርስ እየተሰጠ ይገኛል

የጀርመን ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና እግርኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የአሰልጣኞች የሙያ የማሻሻያ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በጀርመናዊው ኢንስትራክተር ዮሀኪም ፊከርት እና በኢትዮጵያዊው ወጣት አሰልጣኝ ዕድሉ ደረጄ አማካኝነት በሚሰጠው በዚህ ስልጠና ከ15–17 እና ከ20 ዓመት በታች ታዳጊዎችን በማሰልጠን ላይ ለሚገኙ አሰልጣኞች ነው የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እየተሰጠ የሚገኘው።

በመጀመርያው ምዕራፍ ከ200 ሺህ በላይ ስደተኞችን በያዘው በሸርጎሌ ስደተኞች ጣቢያ የሚገኙ የዲሞክራቲንግ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳ እና ሱዳን ዜግነት ያላቸው ከ50 በላይ አሰልጣኞች የተሳተፉበት ስልጠና ለአስር ቀናት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ ባሳለፍነው ረቡዕ ተጠናቋል።

ሁለተኛ ምዕራፍ ስልጠና በዛሬው ዕለት በቤንሻንጉል ክልል አሰሶ ከተማ ከሦስት አውራጃዎች ለመጡ ከ30 ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የአሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት መሠጠት ተጀምሯል።

በኢትዮጵያ በታዳጊዎች ስልጠና ላይ እና በፌዴሬሽኑ በቴክኒክ ኮሚቴ አማካሪነት ለዓመታት እየሰሩ ያሉት ጀርመናዊው ኢንስትራክተር ዮሀኪም ፊከርት ከስልጠናው ባሻገር የስፖርት ቁሳቁሶችን ለሰልጣኞቹ ድጋፍ አድርገዋል።

የቀድሞ ተጫዋች እና በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የአሰልጣኞች ስልጠና በመውሰድ ልምድ እያገኘ የሚገኘው ዕድሉ ደረጄ በዚህ ስልጠና ላይ በመሳተፍ የሚያደርገው ድጋፍ ይበል የሚያሰኘው ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ