ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የሊጉ መሪ ወልዋሎ በሜዳው ጅማ አባጅፋርን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሁለት የተለያየ ጉዞ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ በቡድኖቹ የጨዋታ አቀራረብ ምክንያት አዝናኝ እንቅስቃሴ ይታይበታል ተብሎ ባይገመትም ጥሩ ፉክክር እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል።

ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥብ ሰብስበው በምርጥ ጉዞ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች ምንም እንኳ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ቢያጡም ጨዋታው በወቅታዊ አቋማቸው እና በደጋፊያቸው ፊት እንደመጫወታቸው ይቸገራሉ ተብሎ አይታሰብም።

ጠጣር የመከላከል ክፍል ያላቸው እና በፈጣን መልሶ ማጥቃት የሚጫወቱት ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታም ከባለፉት ጨዋታዎች የተለየ የጨዋታ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ባይጠበቅም በጉዳት ባጧቸው ተጫዋቾች ምክንያት የቋሚ ተሰላፊዎች ለውጥ ማድረጋቸው አይቀሪ ነው።

እንደ ተጋጣሚ አቀራረብ እና የመከላከል አደረጃጀት ተለዋዋጭ የሆነ የማይገመት ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በነገው ጨዋታም ጠጣር የመከላከል ክፍል እና ለተከላካይ ክፍሉ ሙሉ ሽፋን የሚሰጥ አጨዋወት ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ ቡድኑ የሚያጠቃበት መንገድም እንደባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የመልሶ ማጥቃት ላይ መሠረት ያደርጋል ተብሎ ይገመታል።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ አቼምፖንግ አሞስ እና ካርሎስ ዳምጠውን በጉዳት ሲያጡ የፍቃዱ ደነቀ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

በሒደት መሻሻሎች ያሳዩት ጅማ አባ ጅፋሮች በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ምንም እንኳ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ቢገጥማቸውም በጨዋታው ያሳዩት ብቃት ቡድኑ እየተሻሻለ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው። እስካሁን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ ቡድናቸው ያላገኙት አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው በነገው ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታ ጥንቃቄ የተሞላበት እና በጥብቅ የሚከላከል ቡድን ይዘው እንደሚቀርቡ ሲገመት ቡድኑ እንደባለፉት ጨዋታዎች በኤርምያስ ኃይሉ የተመሰረተ የመስመር ማጥቃት አጨዋወትን ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ጨዋታ የሲዳማ ቡና የማጥቃት አጨዋወት ለመቋቋም የተቸገሩት ጅማ አባጅፋሮች የዚህ ሳምንት ተጋጣሚያቸውም በተመሳሳይ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር እና መልሶ ማጥቃትን የሚመርጥ ቡድን እንደመሆኑ ከባለፈው ሳምንት የመከላከል አደረጃጀታቸው ለውጥ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።

ጅማዎች በዚ ጨዋታ የብዙዓየሁ እንደሻው ግልጋሎት አያገኙም ከዚ በተጨማሪም ባለፉት ጨዋታዎች ቡድናቸውን ያላገለገሉት የውጭ ዜጋ ተጫዋቾች ከቡድናቸው ጋር ወደ መቐለ አምርተዋል። ከሲዳማ ጋር በነበረው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ኤርምያስ ኃይሉም በማገገሙ ጨዋታውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ጅማ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሦስቱን በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

– በአራቱ ግንኙነታቸው በአጠቃላይ 7 ጎሎች ሲቆጠሩ ጅማ አምስት፣ ወልዋሎ ሁለት ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ

ምስጋናው ወልደዮሐንስ – ዓይናለም ኃይሉ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ገናናው ረጋሳ – ጠዓመ ወልደኪሮስ

ሰመረ ሀፍታይ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ

ጅማ አባጅፋር (4-3-3/4-5-1)

ሰዒድ ሀብታሙ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሄኖክ ገምቴሳ – ኤልያስ አህመድ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ብሩክ ገብረዓብ – አምረላ ደልታታ


© ሶከር ኢትዮጵያ