በአራተኛው ሳምንት ሁለቱ አዲስ አዳጊዎች ወልቂጤ ከተማ እና ሰበታ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንዲህ ተመልክተነዋል።
ወልቂጤ ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ የሜዳ ጨዋታውን ከከተማው ርቆ በአቢዮ ኤርሳሞ የሚያከናውን ሲሆን ባለፈው ሳምንት ጠንካራው ፋሲል ከነማን በማሸነፍ በጥሩ መነሳሳት ላይ ይገኛል።
በመሰረታዊነት የኳስ ቁጥጥር ላይ ትኩረት የሚያደርጉት ወልቂጤዎች ከሊጉ ጅማሮ በኋላ ግን እንደተጋጣሚዎቻቸው እና እንደጨዋታው ባህርይ የአቀራረብ ለውጥ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ባለፈው ሳምንትም ፋሲል ከነማን በጠንካራ መከላከል ለረጅም ደቂቃዎች መሪነታቸውን አስጠብቀው አሸንፈው መውጣታቸው እንደ ፋሲል ሁሉ ኳስ አብዝቶ ከሚቆጣጠረው ሰበታ ከተማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ሊኖራቸው የሚችለውን አቀራረብ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። በተለይም በመስመር በኩል የጫላ ተሺታን ፍጥነት በመጠቀም የሚደረጉ የማጥቃት ሽግግሮች የቡድኑ መለያ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።
በወልቂጤ በኩል ቶማስ ስምረቱ፣ ፍፁም ተፈሪ እና በማገገም ላይ የሚገኘው ይበልጣል ሺባባው በዚህም ጨዋታ የማይሰለፉ ሲሆን በቃሉ ገነነ ሌላው የቡድኑ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ነው። ባለፈው ሳምንት በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው ኤፍሬም ዘካርያስም በጨዋታው ላይ አይኖርም። ተጫዋች-አሰልጣኙ አዳነ ግርማ ደግሞ ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
በሊጉ በራስ ላይ ከተቆጠረ ግብ ውጪ ጎል ማስቆጠር ያልቻሉት ሰበታዎች ወደ በብዙዎች ወደተገመተላቸው ውጤታማነት ለመመለስ የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የታዩት ጥንካሬዎቻቸውን በሊጉ ለመድገም የተቸገሩት ሰበታዎች በማጥቃት አደረጃጀትና ሽግግሮች ወቅት በግልፅ የሚታዩ ክፍተቶች ተስተውለውባቸዋል። በመከላከሉም ቢሆን በተለይ የጨዋታ ውጭ አቋቋምና በኳስ ምስረታ ወቅት ከተከላካዮች ፊት የሚገኘውን ሰፋፊ ክፍተቶች አጠቃቀም ዙሪያ ድክመት ስለመኖሩ የአዳማው ጨዋታ ፍንጭ የሰጠ ነበር። እንደያዛቸው የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች የፈጠራ አቅም መሀል ለመሀል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የግብ እድልን ለመፍጠር እየተቸገሩ ይገኛሉ።
በአንፃሩ በቀጥተኛ አጨዋወት በተለይም በአጥቂው ባኑ ዲያዋራ ላይ ያነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶች ይበልጥ አደጋ ለመፍጠር የቀረቡ እንደነበሩ መመልከት ችለናል። ምናልባትም ጨዋታው የሚደረግበት የአቢዮ ኤርሳሞ ሜዳ ለጨዋታ አመቺ አለመሆን ቡድኑ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ይበልጥ ረጃጅም ኳሶችን እንዲጠቀም መነሻ ሊሆነው ይችላል።
በሰበታ ከተማ በኩል ለረጅም ጊዜያት ጉዳት ካስተናገደው ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ በቀር ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
የእርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ወልቂጤ ከተማ (4-2-3-1)
ሶሆሆ ሜንሳህ
ዐወል መሐመድ – ዳግም ንጉሴ – መሐመድ ሽፋ – አዳነ በላይነህ
በረከት ጥጋቡ – አልሳሪ አልመሐዲ
ዓባይነህ ፌኖ – ሄኖክ አወቀ – ጫላ ተሺታ
ጃኮ አራፋት
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል አጃይ
ጌቱ ኃይለማርያም – ወንድይፍራው ጌታሁን – አዲስ ተስፋዬ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ
ታደለ መንገሻ – ደሳለኝ ደባሽ – ዳዊት እስጢፋኖስ
ፍፁም ገብረማርያም – ባኑ ዲያዋራ – አስቻለው ግርማ
© ሶከር ኢትዮጵያ