ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

በሊጉ 4ኛ ሳምንት ነገ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል የዐፄዎቹ እና ነብሮቹ ፍልሚያ እንዲህ ተዳሷል።

ፋሲል ከነማ ባለፈው ሳምንት ከሜዳው ውጪ በወልቂጤ ሽንፈት እንደማስተናገዱ ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥቦች በማስመዝገብ ወደ ሰንጠረዡ አናት ፉክክር ለመመለስ አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

ቡድኑ በሜዳው ጠንካራ እና የመጀመርያ የጨዋታ እቅዱን በሙሉ ጉልበት የሚተገብር እንደመሆኑ በጨዋታው ቀዳሚ ተገማች ነው። ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ በሜዳው ቁመት እና ስፋት የተመጣጠነ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግ ቡድን በመሆኑ በተጋጣሚ የኋላ መስመር ቁጥጥር ስር ለመዋል እጅግ ፈታኝ ነው። በተለይም በቀኝ መስመር ያዘነበለው የማጥቃት እንቅስቃሴ የጨዋታው ወሳኝ ነጥብ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ሥዩም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጡ ሲሆን በነገው ጨዋታም ተመራጭ አቀራረባቸውን ይቀይራሉ ተብሎ አይጠበቅም። ይህም በተጋጣሚያቸው ዘንድ ከሚፈጥረው ተገማችነት አንፃር በተቃራኒ የሜዳ ክፍል የመቀባበያ ክፍተት ለማግኘት ሊቸገሩ ይችላሉ።

ፋሲል ከነማ አሁንም ለረጅም ጊዜ በጉዳት ያጣቸው ተጫዋቾችን የማያሰልፍ ሲሆን አቤል እያዩ፣ አብዱራህማን ሙባረክ እና ሰለሞን ሀብቴ ለነገው ጨዋታ መድረሳቸው ቢያጠራጥርም ከጉዳታቸው ማገገማቸው ታውቋል። በወልቂጤው ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት ሽመክት ጉግሳ ለነገው ጨዋታ ብቁ መሆኑ ለቡድኑ መልካም ዜና ነው።

ወደ ፕሪምየር ሊግ ከተመለሰ በኋላ ከሦስቱ ጨዋታዎች ድል ማሳካት ያልቻለው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ጥሩ መስመር ለመግባት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

በስብስብ ደረጃ የተሻሉ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው ቡድኑ ለመዋሀድ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ካለፉት ጨዋታዎች የተስተዋለ ሲሆን ሁነኛ የጨዋታ አቀራረቡንም የለየ አይመስልም። በተለይም በፈጣሪ እና ታታሪ አማካዮች የተዋቀረው የቡድኑ የአማካይ ክፍል በአመዛኙ ውጪ ዜጋዎች ከተዌቀረው የአጥቂ መስመር ጋር ጥሩ ተግባቦት እንዲኖራቸው ማድረግ የአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የቤት ስራ ይሆናል።

ቡድኑ በነገው ጨዋታ የፋሲልን የመቀባበያ አማራጮች በመዝጋት በመልሶ ማጥቃት ነጥብ ይዞ ለመውጣት እንደሚጥር ሲጠበቅ በማጥቃት ወቅት ፋሲሎች ከኋላቸው ትተውት የሚሄዱትን ክፍተት በመጠቀም ረገድ ፈጣን አጥቂዎቻቸው የትኩረት ማዕከል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዞ ወደ ጎንደር ተጉዟል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– የነገው ግንኙነት ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነት ይሆናል።

ቀጥታ ስርጭት

ጨዋታው በአማራ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የሚያገኝ ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሳማኬ ሚኬል

ሰዒድ ሀሰን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ጋብሬል አህመድ – በዛብህ መለዮ

ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – ኦሴይ ማዊሊ

ሙጂብ ቃሲም

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

ታሪክ ጌትነት

ፍራኦል መንግስቱ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቀታ – ሄኖክ አርፍጮ

አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንዳሻው – በኃይሉ ተሻገር

ቢስማርክ አፒያ – መሐመድ ናስር – ኢዩኤል ሳሙኤል


© ሶከር ኢትዮጵያ