ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ

የባለፈው ዓመት የዋንጫ ተፎካካሪዎችን የሚያገናኘው ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በመጀመርያው የሊጉ መርሐ ግብር ላይ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ስድስት ነጥቦች የሰበሰቡት ሲዳማ ቡናዎች የሰመረ አጀማመራቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ባለፉት ጨዋታዎች በመስመር በሚደረጉ ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች እና መልሶ ማጥቃትን መርጠው ወደ ሜዳ የገቡት ሲዳማ ቡናዎች በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ አቀራረብ ይዘው ይገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ የመስመር አጨዋወትም የቡድኑ ሁነኛ የማጥቅያ መንገድ መሆኑ አይቀሪ ነው። ከመስመር አጨዋወታቸውም በተጨማሪ በአማካይ ቦታ ላይ እንደ ዳዊት ተፈራ አይነት ፈጣሪ አማካይ የያዙ በመሆኑ በነገው ጨዋታ የአማካይ ክፍል የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ መሃል ለመሃል የሚሰነዘሩ የማጥቃት አጨዋወቶችም የቡድኑ ሁለተኛ የማጥቅያ መንገድ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።

ሲዳማዎች በነገው ጨዋታ አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩን ጨምሮ ሚልዮን ሰለሞን እና ዮሴፍ ዮሐንስን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ነጥብ ጥለው በሊጉ አራት ነጥብ የሰበሰቡት መቐለዎች ከባለፈው ዓመት ስብስባቸው በአጥቂ ክፍል ላይ ተጨማሪ አቅም ይዘው ወደ ውድድር ቢቀርቡም በአማካይ ክፍል ያላቸው ክፍተት እንዲቸገሩ አርጓቸዋል።

መቐለዎች በቡድናቸው የፈጣሪ አማካይ እጥረት የታየባቸው ሲሆን በተለይም አምበላቸው ሚካኤል ደስታ፣ ዮናስ ገረመው እና ዳንኤል ደምሱን በጉዳት ባጡባቸው ጨዋታዎች በአማራጭ እጥረት የአጨዋወት ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።
በዚህም በሊጉ ጅማሪ እና በቅድመ ውድድር በመስመር ላይ ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት መቐለዎች ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አጨዋወታቸው ወደ ቀጥተኛ እና ረጃጅም ኳሶች ቀይረዋል።

ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታ ሚካኤል ደስታን በጉዳት ሲያጡ ልምምድ የጀመረው ዮናስ ገረመው ወደ ጨዋታ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ እስካሁን ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ጊዜ ድል አርገዋል።

– በግንኙነታቸው ከተቆጠሩት 11 ጎሎች መቐለ ስድስቱን ሲያስቆጥር ሲዳማ አምስቱን አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍስሀ – ሰንደይ ሙቱኩ – ጊት ጋትኮች – ክፍሌ ኪያ

ግርማ በቀለ – ብርሃኑ አሻሞ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – አዲስ ግደይ

ይገዙ ቦጋለ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አሌክስ ተሰማ – አስናቀ ሞገስ

አሸናፊ ሃፍቱ – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – አሚን ነስሩ – ያሬድ ከበደ

ኦኪኪ ኦፎላቢ – አማኑኤል ገብረሚካኤል


© ሶከር ኢትዮጵያ