ነገ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል አዳማ ከተማ ወላይታ ድቻን በሜዳው የሚያስተናግድበት ጨዋታን በዚህ መልኩ ተመልክተነዋል።
ባለፈው ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ የተለያዩት እና ከሦስት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ መሰብሰብ የቻሉት አዳማ ከተማዎች በሶስቱም ጨዋታዎች ግባቸው ሳያስደፍሩ ነበር የወጡት።
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ባሳለፍነው ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር ያለግብ በተለያየው ቡድን ላይ በሁለተኛው ሳምንት ወልቂጤን ከረታው ስብስብ ላይ በአማካይና በተከላካይ ክፍሎች የተደረጉ ለውጦች በርካታ ነበሩ። በተለይም በሶስት የተከላካይ ተጫዋቾችን ሲጠቀም የሰነበተው ቡድኑ በሰበታው ጨዋታ ላይ ወደ 4 ተከላካይ ተሰላፊዎች የመጣ ቢሆንም አሰልጣኙ በእረፍት ሰአት ካደረጉት የተከላካዮች ለውጥ የተነሳ ቡድኑ በዚህ ጨዋታ ዳግም ወደ ሶስት የተከላካዮች ጥምረት እንደሚመለሱ ፍንጭ የሰጠ ሆኗል።
በጨዋታው በተለይ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ላይ ዳዋ ሆቴሳና ከነዓን ማርክነህን በመጠቀም የተቃራኒ ቡድን ኳሶችን መስርተው እንዳይወጡ ለማገድ ጥረት ቢያደርጉም ይህ እንቅስቃሴ በሂደት እየከሰመ መጥቷል። በነገውም ጨዋታ ተጋጣሚያቸው ወላይታ ድቻ እንደ ሰበታ ሁሉ ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ከመሆኑ አንፃር ይህን እንቅስቃሴ በስፋት ሊተገብሩ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዳማ ከተማዎች በዚ ጨዋታ ከጉዳት ተመልሶ ልምምድ የጀመረው ሚካኤል ጆርጅን ጨምሮ ዐመለ ሚልኪያስ እና አማኑኤል ጎበናን በጉዳት አያሰልፉም።
ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባዶ ለባዶ ተለያይተው ወደዚህ ጨዋታ የሚቀርቡት ወላይታ ድቻዎች በሦስት ጨዋታ አራት ነጥቦች ሰብስበው ከተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው ይገኛሉ። ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ጭምር የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ለመጫወት የሚሞክሩት የጦና ንቦች በነገው ጨዋታ ግን እንደባለፉት ጨዋታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ መጫወት ቀላል ይሆንላቸዋል ተብሎ አይገመትም።
ከተጋጣምያቸው የአማካይ ክፍል ጥንካሬ አንፃር በመሃል ሜዳ ቀላል ፉክክር የማይጠብቃቸው ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ ፈጣን አጥቂዎቻቸው እንደ ዋነኛ የማጥቂያ መንገድ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ እንደሆነ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ተስፋዬ አለባቸውን ጨምሮ ሦስት ወሳኝ አማካዮቻቸውን በጉዳት ማጣታቸው ቡድኑ ቀጥተኛ አጨዋወት መርጦ እንዲገባ ያስገድደዋል ተብሎ ይታመናል።
በርካታ ተጫዋቾቻቸው የተጎዱባቸው ወላይታ ድቻዎች ተስፋዬ አለባቸው፣ ያሬድ ዳዊት፣ መክብብ ደገፉ፣ በረከት ወልዴ እና ነጋሽ ታደሰን በጉዳት አያሰልፉም። የደጉ ደበበ እና ባዬ ገዛኸኝ መሰለፍም አጠራጣሪ ሲሆን ቅጣት ላይ ያለው ቸርነት ጉግሳም ቡድኑን አያገለግልም።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 10 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ድቻ 4 አሸንፏል። በቀሪዋ አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በአስሩ ጨዋታ 22 ጎሎች ሲቆጠሩ ሁለቱም እኩል 11 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ግምታዊ አሰለላለፍ
አዳማ ከተማ (3-4-3)
ጃኮ ፔንዜ
መናፍ ዐወል – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ
ፉአድ ፈረጃ – አዲስ ህንፃ – ብሩክ ቃልቦሬ- ከነዓን ማርክነህ
በረከት ደስታ – ቡልቻ ሹራ – ዳዋ ሆቴሳ
ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)
መኳንንት አሸናፊ
ፀጋዬ አበራ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – ይግረማቸው ተስፋዬ
ተመስገን ታምራት
ዘላለም ኢያሱ – እድሪስ ሰዒድ – ፀጋዬ ብርሀኑ – እዮብ ዓለማየሁ
ባዬ ገዛኸኝ
© ሶከር ኢትዮጵያ