ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች የተደረጉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ነገ 9:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ ፍፃሜውን ያገኛል።

ደካማ አጀማመር ያደረጉትና ባለፈው ሳምንት መቐለ ላይ የመጀመርያ ጎላቸውን ማስቆጠር የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ በማግኘት ማንሰራራትን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ከቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ጀምሮ እስከ ሊጉ ጅማሬ ድረስ ከተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ውጪ ይህ ነው የሚባል የሰመረ የማጥቃት አጨዋወት ያልነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በርካታ መሻሻሎች አሳይተዋል። በተለይም በመጀመርያዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች በማጥቃት ሽግግር ላይ በርካታ ክፍተቶች የነበሩባቸው ቡናዎች ባለፈው ከመቐለ ጋር በነበረው ጨዋታ ይህንን ችግር በተወሰነ መልኩ ፈትተው መግባታቸው ቡድኑ ላይ ተስፋ እንዲጣል ቢያደርግም ቡድኑ ተጫዋቾቹ በግል የሚሰሩትን ስህተት ቀንሶ መግባት የግድ ይለዋል።

ከዚ በተጨማሪ ከተለመደው የአሰልጣኙ አጨዋወት ለየት ባለ መንገድ መስመሮችን እንደ ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ ሲጠቀሙ እየተስተዋሉ ያሉት ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው ባህርይ አንፃር በሚያጠቁበት መንገድ ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ቡናማዎቹ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ቡድን ይዘው ለጨዋታው ሲቀርቡ ታፈሰ ሰለሞን ለጨዋታው እንደሚደርስም ይጠበቃል።

ከኢትዮጵያ ቡና በተቃራኒው ጥሩ አጀማመር በማድረግ በሰንጠረዡ አናት ከሚገኙ ክለቦች አንዱ መሆን የቻለው ሀዋሳ ከተማ በነገው ጨዋታም ባለሜዳውን እንደሚፈትን ይጠበቃል።

ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው የአዲሴ ካሳ ቡድን በተለይ ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ላይ ክፍተቶችን የማይሰጥ እና በመልሶ ማጥቃት አደጋን የሚፈጥር ቡድን እንደሆነ ባለፉት ጨዋታዎች ተስተውሏል። የነገው ተጋጣሚው ኳስን በመቆጣጠር በበርካታ ቅብብሎች ወደ ጎል መድረስን የሚመርጥ ከመሆኑ አኳያ በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ መቀባበያ አማራጮች መዝጋትን አልመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል። ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ የሚከላከለው የቡና የተከላካይ መስመር ከኋላው ትቶት የሚሄደው ስፍራን በመጠቀም ረገድ በተለይ ባለፈው ሳምንት ጥሩ ጊዜ ባሳለፉት ዳንኤል ደርቤ እና መስፍን ታፈሰ በኩል በቀኝ መስመር ፈጣን የመልሶ ማጥቃትን ሊተገብሩ የሚችሉበት እድል የሰፋ ነው።

በሀዋሳ በኩል አጥቂው እስራኤል እሸቱ በባህር ዳሩ ጨዋታ በገጠመው ጉዳት የማይሰለፍ ሲሆን ተከላካዩ መሳይ ጳውሎስ አሁንም በጉዳት ከቡድኑ ጋር አልተጓዘም። ተከላካዩ ወንድማገኝ ማዕረግ ደግሞ በቅጣት አይኖርም፡፡

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረበት 1990 ጅምሮ ሳይወርዱ የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች ከየትኛውም ቡድን በበለጠ 42 ጊዜ ተገናኝተዋል።

– የእርስ በእርስ ውጤታቸው በመሀላቸው ያለውን የፉክክር ሚዛናዊነት የሚያሳይ ነው። በእስካሁኑ የ42 ጊዜ ግንኙነታቸውም በ16 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 14 ሀዋሳ ደግሞ 12 ጊዜ ድል አስመዝግበዋል።

– በጥቂት አጋጣሚዎች ካልሆነ በቀር ጎል የማያጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 95 ጎሎች ሲቆጠሩበት ኢትዮጵያ ቡና 52 ጊዜ ኳስ እና መረብን በማገናኘት የበላይ ነው። ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሦስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 43 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተ/ማርያም ሻንቆ

አሕመድ ረሺድ – ወንድሜነህ ደረጀ – ፈቱዲን ጀማል – አሥራት ቱንጆ

ዓለምአንተህ ካሳ – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሰ ሰለሞን

አቡበከር ናስር – እንዳለ ደባልቄ – አቤል ከበደ

ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1/4-5-1)

ቤሌንጋ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – ተስፋዬ መላኩ – ላውረንስ ላውንቴ – ኦሊቨር ኩዋሜ

አለልኝ አዘነ – ዘላለም ኢሳይያስ

ብርሃኑ በቀለ – ሄኖክ አየለ – መስፍን ታፈሰ

ብሩክ በየነ


© ሶከር ኢትዮጵያ