አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻ ያገናኘው የአራተኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ውጤቱ እንቅስቃሴያችንን አይገልፀውም” የአዳማ ከተማ ም/አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል
የጨዋታው እንቅስቃሴ
ከመጀመርያው ጀምሮ ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ነበር የሞከርነው። ብልጫ የነበረን ቢሆንም ኳስ በመሆኑ ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል። ውጤቱ እንቅስቃሴያችንን አይገልፀውም፤ ከፍተኛ ብልጫ ነበረን። በጥቃቅን ስህተት በተለይ ከትኩረት ማነስ በተፈጠረ ክፍተት ጎሎች ገብተውብን ጨዋታውን አጠናቀናል። ምንም ማድረግ አይቻልም።
የቡድኑ ተጫዋቾች ልምምድ ማቋረጥ
ምንም የፈጠረብን ተፅእኖ የለም። ከእርሱ ጋር ምንም የሚገናኝ ነገር የለውም። ሜዳ መጥተን ልምምድ አንስራ እንጂ እኛ በራሳችን መንገድ ልምምዳችንን በአግባቡ እየሰራን ቆይተናል። በዛሬው ጨዋታ አሸንፈን መውጣት የምንችልባቸው አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን ነው ነጥብ ተጋርተን እንድንወጣ ያደረገን።
“እኔ በህይወቴ የትም ሜዳ ለአቻ ተጫውቼ አላውቅም”። የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ
ስለ ጨዋታው
ከእረፍት በፊት በእኛ ተጫዋቾች በኩል አለመረጋጋት ነበር። ከእረፍት በኃላ ግን የተሰጣቸውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ተጫዋቾቼ ጥረት አድርገዋል። በዚህም እንቅስቃሴ ከመመራት ተነስተው መምራት ችለውም ነበር። ኋላ ላይ ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቅ እንጂ። ይህ ውጤት ለእኛ ጥሩ ነው። ምክንያቱም የቡድኑ ስድስት ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾች ዛሬ በጉዳት አልተጫወቱም። ስለዚህ ተጫዋቾቼ ያሳዩት ነገር ለእኔ በጣም ጥሩ ነበር።
ተከታታይ አቻ መውጣት
እኔ በህይወቴ የትም ሜዳ ለአቻ ተጫውቼ አላውቅም፤ የምታዩት ነው። ዛሬም 4-3-3 የጨዋታ አሰላለፍ ይዤ ነው ለማጥቃት ስጫወት የቆየሁት። ነገር ግን የሀገራችን እያንዳንዱ ሜዳዎች የተለያዩ ደረጃዎች መኖራቸው ተጫዋቾች የፈለጉትን እንቅስቃሴ እንዳይተገብሩ አድርጓቸዋል። ከእረፍት በኋላ ከመመራት ተነስተን መምራት ችለን ነበር። አቻ ብንፈልግ ኖሮ የተከላካይ ቁጥራችንን አብዝተን ተከላክለን ውጤት አስጠብቀን እንወጣ ነበር። ሆኖም ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ነበር ስንቀሳቀስ የቆየነው። ምክንያቱም አንድ ጎል አስተማማኝ ባለመሆኑ።
© ሶከር ኢትዮጵያ