የሊጉ መሪ ወልዋሎ እና ጅማ አባጅፋርን ያገናኘው የአራተኛ ሳምንት ጨዋታ ትግራይ ስታዲየም ላይ ተከናውኖ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በርካታ የግብ ሙከራዎች በታየበት ጨዋታ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት ስሑል ሽረን ከረታው ስብስብ ፍቃዱ ደነቀ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና አቼምፖንግ አሞስን አስወጥተው በኄኖክ መርሹ ፣ሰመረ ሀፍታይ እና ሚካኤል ለማ ተክተው ሲገቡ ጅማ አባጅፋሮች በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገደው ስብስባቸው አምረላ ደልታታን አስወጥተው ጀሚል ያዕቆብን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ መልሰው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ያልተገመቱ የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ውሳኔዎች በታየበት ጨዋታ አማካዩ ገናናው ረጋሳ በመሃል ተከላካይነት ጨዋታውን ሲጀምር ሄኖክ መርሹ በተከላካይ አማካይነት ተሰልፎ ጨዋታውን ጀምሯል።
ወልዋሎዎች ተሽለው በታዩበት የመጀመርያው አጋማሽ በባለሜዳዎቹ በኩል በርካታ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። ከነዚህም ሚካኤል ለማ አሻምቷት ጁንያስ ናንጂቡ ያደረጋት ጥሩ ሙከራ እና ሰመረ ሀፍታይ በሁለት አጋጣሚዎች በግንባር ያደረጋቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
በጨዋታው ከሁለቱም መስመሮች ወደ ሳጥን በሚሻሙ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ወልዋሎዎች በተጠቀሰው አጨዋወት በርከት ያሉ ዕድሎች ቢፈጥሩም በተጋጣሚ ሳጥን በተወሰደባቸው የቁጥር ብልጫ እንደሚጠበቀው ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም።
በአጋማሹ የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት በተሳካ ሁኔታ ከማምከን ውጭ ይህ ነው የሚባል ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያላሳዩት ጅማ አባጅፋሮች ምንም እንኳ በርካታ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም በጥቂት አጋጣሚዎች ጥሩ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ከነዚህም ኤልያስ አሕመድ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ያደረጋት ሙከራ እና ጀሚል ያዕቆብ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ዓብዱልዓዚዝ ኬታ እንደምንም ሲያድናት የተተፋችው ኳስ መስመሩን ከማለፏ ገናናው ረጋሳ ደርሶ ያወጣት ሙከራ በእንግዶቹ በኩል የምትጠቀስ ወርቃማ ዕድል ናት።
ብዙም ሳቢ ያልነበረው እና ከመጀመርያው አጋማሽ በቁጥር እጅግ ያነሱ የግብ ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ነበር። በአጋማሹ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ወልዋሎዎች ሲሆኑ ሙከራውም በሰመረ ሀፍታይ አማካኝነት የተደረገ ነበር። ወልዋሎዎች ከተጠቀሰው ሙከራ ውጭም በራምኬል ሎክ፣ ጁንያስ ናንጂቦ እና በብሩክ ሰሙ አማካኝነት የግብ ዕድሎች የፈጠሩ ሲሆን በተለይም ጁንያስ ናንጂቦ ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻማለትን ኳስ በግንባር ሞክሮ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ስዒድ ሀብታሙ እንደ ምንም ያወጣት ኳስ ወልዋሎን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ጥሩ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ጅማ አባጅፋሮችም በተለይም በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በሀብታሙ ንጉሴ፣ ጀሚል ያዕቆብ እና ሱራፌል ዓወል ያደረጓቸው ሶስት ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በተለይም ጀሚል ያዕቆብ አክርሮ መቷት ዓብዱላዚዝ ኬታ ያዳናት እና ሀብታሙ ንጉሴ በጥሩ ሁኔታ መቷት ግብ ጠባቂው እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ በተሻለ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
ውጤቱን ተከትሎ ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያሸነፉት ወልዋሎዎች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ ሲጥሉ ጅማ አባጅፋሮች በዓመቱ ለሦስተኛ ጊዜ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ