የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ 0-0 ጅማ አባ ጅፋር

የሊጉ መሪ ወልዋሎ በሜዳው ከጅማ አባጅፋር ጋር ባዶ ለባዶ አቻ መለያየቱ ይታወሳል። የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞችም ከጨዋታው በኋላ የሚከተለው ሃሳብ ሰጥተዋል።

“ከነሱ የተሻሉ ብዙ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል” ዮሐንስ ሳህሌ – ወልዋሎ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። አንዳንድ ጨዋታዎች ጎል አይገኝባቸውም። አንዳንድ ተሻጋሪ ኳሶች ዒላማ የሌላቸው ነበሩ ብዙ ኳሶች አበላሽተናል። የማሸነፍ ጉጉት ስለነበር መረጋጋት አልነበረም እነዚ እነዚ ክፍተቶች ነበሩብን፤ ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን።

ቡድኑ ስላልተጠቀመባቸው የግብ ዕድሎች

ከነሱ የተሻሉ ብዙ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል። ከምንም በላይ ግን ተረጋግተን የምናገኛቸውን ኳሶች ለሚገባው ሰው መስጠት ላይ ክፍተት ነበር። እነሱ አፈግፍገው ነበር የተጫወቱት። ያ ሲሆን ኳሱን ይዘን መጫወት እና ጎል አካባቢም ከሳጥን ውጭ መምታት እንችል ነበር ለቆሙ ተጫዋቾች ኳሶች ከምናሻግር።

“ጨዋታው ሚዛናዊ ነበር” ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባ ጅፋር

ስለ ጨዋታው

ተጋጣሚያችን ከማሸነፍ እኛ ደግሞ ከመሸነፍ ነበር የመጣነው። ሊጉን እየመራ የሚገኝ ቡድን ነው የገጠምነው። እኛ ደግሞ አንዳንድ ነገሮች ያላለቁልን አሉ፤ ሶስት የውጭ ተጫዋቾቻችን በዚህ ጨዋታ አልተካፈሉም። ተጫዋቾቻችንም ገና ወጣቶች ናቸው።

ጨዋታው ሚዛናዊ ነበር እኛ አጭር ኳስ እነሱ ደግሞ ረጅም ኳስ መርጠው ነበር የገቡት። የነሱን ረጃጅም ኳሶች ለማቆም ያደረግነው ሙከራ ተሳክቶልናል። እንደውም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያገኘናቸው ዕድሎች አልተጠቀምንም እንጂ አሸንፈን መውጣት እንችል ነበር።

ስለ ቡድኑ አጨዋወት

ተጋጣሚያችን ረጃጅም ኳስ በመምረጥ በሁለት እና በሶስት ንክኪ ነበር ወደ ጎል የሚደርሱት። ቡድናችን ደግሞ ኳስን ከኃላ መስርቶ በመውጣት መሐል ሜዳ ላይ ችምችም ብለን በመጫወት በመስመሮች ነበር ስናጠቃ የነበረው። ቡድኑ ተፈጥሯዊ አጥቂ የለውም፤ አጨዋወታችን እየዳበረ የሚሄድ ነው። ቀጣይ ከወጣት ተጫዋቾቻችን ብዙ ጥሩ ነገር ታያላችሁ።

አራት ጨዋታ አድርገን አራቱም ከሜዳችን ውጭ ነው ያደረግነው። ተጫዋቾቹ ብዙ ልምድ የሌላቸው ናቸው። በአጠቃላይ ባመጣኋቸው ተጫዋቾች ደስተኛ ነኝ።


© ሶከር ኢትዮጵያ