ኢትዮጵያዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አዲስ ህንፃ በሱዳን ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታ ክለቡ አልሃሊ ሸንዲ አል ሜሪክ ኒያላ ላይ የማሸነፊያ ግብ አስቆጥሯል፡፡
በሸንዲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሸንዲ በአዲስ ግብ ታግዞ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ የውል ማራዘሚያ ለሸዲን የፈረመው ተጫዋቹ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ግቡ ነች፡፡
ዘጠኝ ነጥብ በመያዝ መሪዎችን አል ሂላል እና አል ሜሪክን የተጠጋው ሸንዲ በመጪው ሐሙስ ከሊጉ መሪ አል ሂላል ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከወዲሁ ትኩረትን ስቧል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 1 ብቻ ነው፡፡ የሱዳን ፕሪምየር ሊግ በ18 ክለቦች መካከል ሲደረግ የዓምና ሻምፒዮኑ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ግማሽ ተፋላሚ የነበረው አል ሜሪክ ነው፡፡ ሸንዲ ዓምና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ያጠናቀቀ ሲሆን በካፍ ኮንፌድሬሽን ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡
የኡመድ ኡኩሪ ከኤንፒፒአይ ቡድን ውጪ መሆን የተለመደ ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡ ኡመድ ክለቡ ኢኤንፒፒአይ ከምስር አል ማቃሳ ጋር 1-1 በተለያየበት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ከቡድኑ ውጪ ነበር፡፡
በፔትሮ ስፖርት ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ለኤንፒፒአይ አህመድ ሽርሚዳ ሲያስቆጥር ለአል ማቃሳ ቅዳሜ የመከላከያ ተከላካዮችን ይፈትናል ተብሎ የሚጠበቀው ጋናዊው ናና ፖኩ ከመረብ አዋህዷል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ የኡመድ በተደጋጋሚ ከቡድኑ ውጪ መሆንን ለማጣራት ያደረችው ጥረት አልተሳካም፡፡
ሽመልስ በቀለ ባልተሰለፈበት ጨዋታ ፔትሮጀት ከሜዳው ውጪ ኢትሃድ ኤል ሾርታን 1-0 አሸንፏል፡፡ የአጥቂ አማካዩ ሽመልስ ተቀያሪ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታው ተመልክቷል፡፡ ታላት የሱፍ የአሰልጣኝነት መንበሩን ከአህመድ ሃሰን ከተቀበሉ በኃላ ሽመልስ በቂ የመሰለፍ ዕድል እየተሰጠው አይደለም፡፡
የፔትሮጀትን የድል ግብ የቀድሞ የዛማሌክ አጥቂ አህመድ ጋፍር በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡ ጋፍር በውድድር ዓመቱ ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
በግብፅ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዣን በተጠባቂው የካይሮ ደርቢ ዛሬ የሚፋለሙት የምንግዜም ተቀናቃኞቹ አል አሃሊ እና ዛማሌክ በ35 እና 31 ነጥብ ሲመሩ ፔትሮጀት ደረጃውን አሻሽሎ በ26 ነጥብ 6ኛ ነው፡፡ አንድ ቀሪ ጨዋታ የሚቀረው ኢኤንፒፒአይ በ22 ነጥብ 9ኛ ነው፡፡
የዋሊያዎቹ የፊት አጥቂ ጌታነህ ከበደ ክለቡ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ባደረጋቸው ሁለት የአብሳ ፕሪምየርሺፕ ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል፡፡ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ዕረቡ ከፍሪ ስቴት ስታር ጋር 2 አቻ በተለያየበት ጨዋታ ናኮናን በ70ኛው ደቂቃ ቀይሮ ገብቷል፡፡
ለፕሪቶሪያው ክለብ ታቦ ማንያማኔ ሁለቱንም ግቦች ሲያስቆጥር ለስታርስ ዳኒ ቨንተር እና ሴሎ ጃፕታ ግብ ማግባት ችለዋል፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ በተደረገ የፕሪምየርሺፑ ጨዋታ አማተክስ በኦርላንዶ ፓይሬትስ 1-0 ሲሸነፍ ጌታነህ አሁንም በድጋሚ ናኮናን በ62ኛው ደቂቃ ቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል፡፡
ለፓይሬትስ የድል ግቡን ታቦ ማትላባ በ70ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡ አማተክስ በደረጃ ሰንጠረዡ በ13 ነጥብ 15ኛ ላይ ሲሆን ሊጉን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በ42 ነጥብ ይመራል፡፡