“ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ አዲስ ነገር እናሳያለን ብለን እናምናለን” – እንዳለ ደባልቄ

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ባህር ዳር ከተማን ለቆ የካሣዬ አራጌውን ቡድን የተቀላቀለው አጥቂው እንዳለ ደባልቄ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እንደ ቡድን የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገር በነበረው ቡድን ግብ ለማስቆጠር ተቸግሮ ቢቆይም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እያሳየ በሚገኘው ቡድን ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመሪያ ግቡን ያስቆጠረው እንዳለ በ4ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታ ብልጫ ጋር ሀዋሳ ከተማን ሲረታ ደምቆ መዋል ችሏል።

በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራው አጥቂው እንዳለ ደባልቄ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተፈጠረበትን የደስታ ስሜትና እቅዱ በተከታዩ መልኩ ለመገናኛ ብዙሃን አጋርቷል።

ስለ ጨዋታውና ሐት-ትሪክ ስለመስራቱ

“በየጨዋታው ሁሉ ግቦችን ማስቆጠርን አስባለው፤ ዛሬ ፈጣሪ ረድቶኝ ይህን ማሳካት ችያለሁ። ከቡድን አጋሮቼ የቀረቡልኝ ኳሶች ዛሬ በአግባቡ ተጠቅሚያለሁ ብዬ አስባለሁ። በአሰልጣኛችን በተሰጠን ትዕዛዝ መሠረት እንደቡድን ዛሬ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለናል።”

ስለቡድናቸው ጠንካራ ጎን

“ሁሌም ቢሆን በውስጣችን የማሸነፍ ስሜት አለ። ሁሌም ወደ ሜዳ ስንገባ የራሳችን የሆነ የተለየ የአጨዋወት መንገድ አለን። ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሌም ቢሆን ጥረት እናደርጋለን፤ በዚህ መሀል ማሸነፍ መሸነፍ ያለ ነው። ከሶስት ጨዋታዎች በኃላ ዛሬ ድል ቀንቶናል፤ ከዚህ በኃላ ባሉ ጨዋታዎች ደግሞ በተሻለ መነቃቃት ለማሸነፍ እንጫወታለን።”

ለዚህ ቡድን ስለመጫወትና ግብ ማስቆጠር ስለሚሰጠው ስሜት

” ከልጅነቴ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት ሳልመው የነበረ ነገር ነው፤ ይህንንም ዘንድሮ ማሳካት ችያለሁ። በዚህ መለያ ግብ ማስቆጠር ከፍተኛ ደስታ ይፈጥራል። ፕሪምየር ሊጉ የአንድ ጨዋታ ብቻ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ ዛሬ ስላሸነፍን ብቻ ደስታችንን አንገልፅም። ዓመቱን ሙሉ ከዚህ በተሻለ አሰልጣኛችን በቀጣይ በሚሰጠን ስልጠና ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ አዲስ ነገር እናሳያለን ብለን እናምናለን።”

ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ስለመጨረስ

“በግሌ ይህን ያህል ጎል አገባለሁ አልልም፤ ምክንያቱም እንቅስቃሴያችን እንደቡድን ነው የሚተገበረው። ዋነኛው ዓላማዬ አሰልጣኙ የሚሰጠኝን ተልዕኮ መወጣት ነው። በዚህ መሀል ግቦችን ማስቆጠር የምችል ከሆነ ግቦችን በማስቆጠር ቡድኔን ማገዝ ዋነኛ እቅዴ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ