አስተያየት – አብርሃም ገ/ማርያም እና ሚካኤል ለገሰ

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ እና ሰኞ በክልል ስታዲየሞች ተከናውነው መሪው አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጪ በድሬዳዋ ከተማ 2-0 ተሸንፎ መሪነቱን አርባምንጭን አሸንፎ ለተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያስረክብ ሶስት ተጫዋቾች የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት በጋራ መምራት ጀምረዋል፡፡    

በ9ኛው ሳምንት በተካሄዱት ጨዋታዎች ከታየው የፉክክር መንፈስ ፣ የአዳማ ከተማ መንሸራተት ፣ ሁሉም ጨዋታ ባልተለመደ ሁኔታ ከአዲስ አበባ ውጭ መካሄድ እና የክለቦች የሚዋዥቅ አቋም ይልቅ ትኩረት የሳበው በተለዩ ከተሞች የነበሩት ጨዋታ ለረጅም ደቂቃ ለማቋረጥ የሚያስገድዱ የደጋፊዎች ብጥብጥ ፣ ስርአት አልበኝነት እና በጨዋታ ሒደት የሚከሰቱ ክስተቶችን አምኖ አለመቀበል ነበር፡፡ ከ9ኛው ሳምንት መጠናቀቅ በኋላ ስለ ጨዋታዎቹ እንቅስቃሴ ፣ ውጤቱ በቀጣይ ጨዋታ ስለሚያስከትለው ተጽእኖ እና የመሳሰሉ እግርኳሳዊ ወሬዎች ከማውራት ይልቅ ስለተከሰተው ብጥብጥ ማውራት እግርኳሳችን ያለበትን ደረጃ የሚያመለክት ነው፡፡

የተመልካች ረብሻ ፣ የዳኛ ውሳኔን ተከትሎ የሚመጣ ውዝግብ እና የመሳሰሉት ክስተቶች ለኢትዮጵያ እግርኳስ አዲስ ባይሆኑም በዚህ ሳምንት ድግሞ ተባብሶ ታይቷል፡፡

በሀዋሳ ስታድየም በኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች መካከል የተነሳው ብጥብጥ ጨዋታው ለ30 ደቂቃዎች እንዲቋረጥ መንስኤ ሆኗል፡፡ ግርግሩን ለማስቆም ልዩ ሃይል እስኪመጣም ተጠብቋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ባደረጉት ጨዋታ ደግሞ አዳነ ግርማ ያስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠበት አግባብ ላይ የተነሳው ቅሬታ መልኩን ቀይሮ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጧል፡፡ በሆሳዕና መከላከያን የገጠመው ሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ ሰአት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በማምከናቸው ምክንያት ደጋፊው ተቆጥቶ ተጫዋቾች ከሜዳ እንዳይወጡ እስከመከልከል ደርሰዋል፡፡

በኢትየጵያ እግርኳስ ሰር ከሰደዱ ችግሮች ዋንኛው የሆነው ይህ የስታድየም ረብሻ ፣ የትኛውንም የዳኛ ውሳኔ ያለመቀበል ፣ ክብር የሚነኩ ዘለፋዎች ፣ የተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ለፀብ የሚያነሳሱ ድርጊቶች ለስታድየሞቻችን ከስማቸው ጋር አብሮ የተሰጠ እስኪመስል ድረስ ተለምዷል፡፡ በስታድየሞቻችን እነዚህን አፀያፊ ስድቦች እና ፀብ አነሳሽ ድርጊቶች ከትልልቅ ሰዎች የሚመለከቱ ህጻናት ሲተገብሩ መመልከት ለመቀበል ቢከብድም አሁን አሁን የተለመደ የእለት ተእለት ተግባር ሆኗል፡፡ እግርኳስ አፍቃርያን የወንድማማችነት እና የመግባባት ምሳሌ የሆነው ንፁህ እግርኳስን የሚበክሉ ድርጊቶች እየተመለከቱ ጨዋታ ለመመልከት ወደ ካምቦሎጆ የሚያመሩበት ምክንያት የለም፡፡ ስታድየሞቻችን ለህፃናት ፣ በእድሜ ለገፉ ሰዎች ፣ ሴቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ተመራጭ ያልሆነ ስፍራ እየሆነ መምጣቱና አዳዲስ ተመልካች የማይጋብዝ እግርኳስ ባለቤት መሆናችን ሊያሳስበን ይገባል፡፡

የስታድየም ብጥብጥ እና ከተመልካች የሚሰነዘሩ ፀያፍ ቃላት በአንድ ጀንበር ከእግርኳሳችን ይጠፋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ችግሮች የሚቀንሱ ስራዎች የመስሪያቸው ጊዜ አሁን ነው፡፡

ስታድየሞች ለጨዋታ ተስማሚ ሆነ ሜዳ ብቻ ሳይሆን ለተመልካችም የተመቹ እንዲሆኑ የሚያስገድድ ደንብ ከፌዴሬሽኑ ይጠበቃል፡፡ በክልል ስታድየሞች የተለመዱት ለጸብ የተመቹ ድንጋይ እና ከግንባታ የተረፉ ቁሳቁሶች ሊወገዱ ይገባል፡፡ ሜዳንና ተመልካቹን የሚለይ አስተማማኝ አጥር ሊኖር ይገባል፡፡ ሜዳ እና ተመልካችን ብቻ ሳይሆን መንገድ እና ስታድየሙን የሚለይ አጥር በማጠር ከውጭ ወደ ስታድየሙ በሚወረወሩ ቁሳቁሶች ደጋፊ እንዳይጎዳ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡

ደጋፊዎችን ለፀብ የሚጋብዙ የዳኝነት ውሳኔዎች ለመቀነስ ፌዴሬሽኑ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ለዳኞች ተከታታይ ስልጠናዎች ሊሰጥና ጨዋታን እና የደጋፊ ተጽእኖን የሚቆጣጠሩበት ጥበብ ሊያስተምራቸው ይገባል፡፡ ከዳኞች በተጨማሪም ደጋፊን የሚያነሳሱ ስርአት አልበኛ ተጫዋቾችን የሚገራ እና ከውሳኔ በኋላ ዳኛን የማዋከብ ድርጊቶችን ገደብ የሚያበጅለት ደንብ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡

የፀጥታ አካላት ከፌዴሬሽኑ ጋር ተግባብተው የሚሰሩበት ጊዜ አሁን መሆን አለበት፡፡ መደበኛ የፀጥታ አስከባሪዎች እና ተመልካቹ የማይግባቡበት ወቅቶች እልፍ እንደመሆናቸው በሌላው አለም እንደሚሰራበት ከፖሊስ ሃይል ጋር በጋራ የሚሰራ ተጨማሪ አካል (Stewards) በስታድየም ሊኖር ይገባል፡፡ በበሮች የሚደረገው ፍተሻም የቁሳቁስ ብቻ ከመሆን አልፎ ከመጠን በላይ ጠጥተው የሚመጡ ግለሰቦች ዘልቀው እንዳይገቡ የሚቆጣጠር አሰራር ሊዘረጉ ይገባል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን በተለይም ከፍተኛ ተከታታይ ያላቸው የቴሌቪዥን እና ሬድዮ የስፖርት ፕሮግራሞች ደጋፊዎች ወደ ብጥብጥ እንዳያመሩ የሚያስገነዝብ ስራ ሊሰሩ ይገባል፡፡ ተመልካቹ በስታድየም የሚገኝበትን አላማ እንዳይስት እና የኳስ መንፈስ ብቻ እንዲኖረው የማድረግ አቅም ያለው ሚድያ ነው፡፡ የስፖርት ፕሮግራሞች አላማ ገበያ ሳቢነት ብቻ ሳይሆን እግርኳሳችን በሚድያዎች ሊያገኝ የሚገባውን ትኩረት መስጠት ጭምር ነው፡፡

በስታድየም ዙርያ (በተለይም በአዲስ አበባ ስታድየም) ተሰግስገው የሚገኙት መጠጥ ቤቶች ለስሜታዊ ደጋፊዎች መፍለቂያ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ በሌላው አለም በስታድየም ውስጥ ጭምር አልኮል መጠጦች ቢሸጡም የደጋፊው ከፍ ያለ የንቃተ ህሊና ደረጃ ፣ አስተማማኝ የጥበቃ ስርአት ፣ የእግርኳሱ የጥራት ደረጃ እና የመሳሰሉት ሁኔታዎች ደጋፊዎች ወደ ብጥብጥ እንዲያመሩ አይጋብዝም፡፡ ጥናቶች ቢፈልግም በኢትዮጵያ የደጋፊዎች ብጥብጥ ከአልኮል መጠጦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እንደሆነ ግልጽ እንደመሆኑ መጠን ቢያንስ ቢያንስ የመጠጥ መሸጫ ቤቶች ከስታድየም ራቅ ባለ ቦታ የሚሸጡበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የስታድየም ብጥብጥ እና ሁከት በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት እግርኳሳችን ከዚህም በከፋ ሁኔታ ወደ መቀመቅ የማይወርድበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ፌዴሬሽን ፣ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች ፣ ደጋፊዎች ፣ የፀጥታ አካላት፣ መንግስት እና የመገናኛ ብዙሃን የየበኩላቸውን በመወጣት የእግርኳሱን ዋንኛ ችግር ማስወገድ አልያም መቀነስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ያጋሩ