የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ለገጣፎ እና ዓድዋ ተከታታይ ድላቸውን ማስመዝገብ ችለዋል። ኤሌክትሪክ እና ደሴ ከተማም አሸንፈዋል።
በምድቡ ተጠባቂ የነበረውና የአንደኛ ሊግ ጨዋታ በጊዜ አለመጠናቀቁን ተከትሎ ከሌሎች ጨዋታዎች እጅጉን ዘግይቶ የጀመረው የለገጣፎ ለገዳዲ እና አክሱም ከተማ ያረጉት ጨዋታ በጣፎዎች 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ለገጣፎዎች በ16ኛው ደቂቃ ዳዊት ቀለመወርቅ ግብ አስቆጥሮ መሪ በመሆን ወደ እረፍት ያመሩ ሲሆን በ58ኛው ደቂቃ ሽመክት ግርማ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት ሐት-ትሪክ በሰራው ልደቱ ለማ አማካኝነት በ75ኛው ደቂቃ በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-0 አሸንፈዋል።
ከጫዋታ ባኋላ የአክሱም ከተማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክንፈ ለሶከር ኢትዮጽያ “የተደረገው ነገር ትክክል አይደለም፤ እኛ ሰዓታችንን ጠብቀን ነው የተገኘነው። ነገር ግን ሜዳው በሌላ ጨዋታ ተይዞ ነበር። ይህን ብናውቅ ኖሮ አመጋገባችን እና ለጨዋታው የምናደርገውን ዝግጅት እናስተካክል ነበር።” በማለት ቅሬታቸውን ገልፀዋል።
ዓድዋ ላይ ሶሎዳ አድዋ ወልዲያን አስተናግዶ ከመመራት በመነሳት ሦስት ነጥቦች መሰብሰብ ችሏል። ወልዲያዎች ወደ እረፍት ከማምራታቸው በፊት በጭማሪ ደቂቃ ላይ ፉዐድ ጀማል ባስቆጠረው ጎል መሪ መሆን ቢችሉም ከእረፍት እንደተመለሱ ኤፍሬም ኃይለማርያም እንዲሁም ኃይሉሽ ፀጋይ በ72ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች አዲስ አዳጊዎቹ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሜዳው ወሎ ኮምቦልቻን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ አራት አሳድጓል። የቀዮቹን ብቸኛ ጎል ሀብታሙ መንገሻ ማስቆጠር ችሏል።
ደሴ ላይ ደሴ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን አስተናግዶ 2-0 በማሸነፍ የመጀመርያ ድሉን አሳክቷል። አጥቂዎቹ በድሩ ኑርሁሴን እና አኩዌር ቻም ከእረፍት በፊት ያስቆጠሯቸው ጎሎች ለባለቅኝቶቹ ሦስት ነጥብ አስገኝተዋል።
በዚህ ምድብ የተደረጉት የፌዴራል ፖሊስ እና ደደቢት እንዲሁም የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና ገላን ከተማ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርባቸው በተመሳሳይ 0-0 ተጠናቀዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ