የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ አምስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ ሀላባ ከተማ እና ሀምበሪቾ ድል አስመዝግበዋል። ቀሪዎቹ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
መከላከያ 0-0 ነቀምቴ ከተማ
(በዳንኤል መስፍን)
ጃንሜዳ ጀርባ በሚገኘው የመከላከያ ሜዳ መከላከያ እና ነቀምቴ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
መከላከያ ከ2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ ባስመዘገበው ዝቅተኛ ነጥብ ወደ ከፍተኛ ሊግ በመውረዱ ዳግም ወደ ሊጉ ለመመለስ ከቡድኑ ጋር ዓምና ሲጫወቱ የነበሩ አብዛኛውን ነባር ተጫዋቾችን በማቆየት እና አዲስ ጠንካራ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ራሱን አደረራጅቶ ለውድድሩ ቀርቧል። ከ2011 ጀምሮ ከራሱን አሻሽሎ በመቅረብ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ብርቱ ትግል ያደረገው እና ዘንድሮ በተመሳሳይ አቋም የሚገኘው ነቀምቴ ከተማም ጥሩ ቡድን በመስራት ለውድድሩ ተዘጋጅቷል።
ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ጎል በመድረስም የጎል እድል በመፍጠር የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች በፍቃዱ ዓለሙ አማካኝነት ግልፅ የጎል ዕድል በመፍጠር ሳይጠቀሙበት በቀረው የጎል ሙከራቸው ጅማሬ ባደረገው አጨዋወታቸው በተለይ 13ኛው ደቂቃ ሽመልስ ተገኝ ከቀኝ መስመር ወደ ጎል ያሻገረለትን ከተስፋ ቡድን ዘንድሮ ያደገው መሐመድ አበራ በነፃ አቋቋም በግንባሩ ገጭቶ የውጭ መረብን ነክቶ ወደ ውጭ የወጣው ኳስ ለመከላከያ መሪ ማድረግ የሚችል እድል ነበር።
በነቀምቴ በኩል በተደራጀ አጨዋወት አደገኛ እድሎች ባይኖርም አልፎ የሚፈጥሩት የጎል አጋጣሚ ለመከላከያ ተከላካዮች የሚያስጨንቁ ነበር። በተለይ በፍጥነት እስራኤል ታደሰ በጥሩ ሁኔታ ከመስመር ያሻገረውን በዕለቱ በነቀምቴ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዋቁማ ድንሳ ወደ ጎል መቶት ለጥቂት የወጣበተት ከሚያደርጓቸው ሙከራዎች አንዱ ነበር።
መከላከያ ኳሱን መስርተው ለመጫወት ሲያስቡ ነቀምቴዎች ምንም ዓይነት ክፍተት ባለመፍጠር አፍነው በመጫወት የመከላከያን አጨዋወት ሲያበላሹ ቆይተዋል። ይህም ቢሆን መከላከያዎች በ31ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ዓለሙ ከመሐል ሜዳ የተጣለለትን ፍጥነቱን ተጠቅሞ አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ ገብቶ ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ኢብሳ አበበ አድኖት የተፋውን ከተስፋ ቡድን ዘንድሮ መከላከያን የተቀላቀለው ተፈራ አንለይ ነፃ ኳሰ አግኝቶ አገባው ሲባል ግብጠባቂው ኢብሳ ከወደቀበት በድጋሚ ተነስቶ በሚገርም ሁኔታ ያዳነው መከላከያዎችን መሪ ማድረግ የሚችል ሌላ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነው።
ከእረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ በጥንቃቄ መጫወት የመረጡት ነቀምቴዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጨዋታውን በማዘግየት የመከላከያን እንቅስቃሴ አቀዝቅዘውታል። ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት የተጋጣሚያቸው አጨዋወት አልፈቅድ ያላቸው መከላከያዎች በቆሙ ኳሶች እና በረዣዥም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ ተገደዋል። በዚህም እንቅስቃሴ በሁለት አጋጣሚ ተከላካይ አበበ ጥላሁን በግንባሩ በመግጨት የሞከረው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።
አብዛኛው የጨዋታ ደቂቃዎች በተለይ በነቀምቴ በኩል አላስፈላጊ በሆነ ሰዓት የማባከን እንቅስቃሴ ተጠምደው ጨዋታው ሲቆራረጥ ቆይቷል። ከጠንካራ ቡድን ጋር እንደመጫወታቸው አቻውን የፈለጉት ነቀምቴዎች ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ፀጋአብ ብርሀኑ ጥሩ ኳስ አግኝቶ በሚገር ሁኔታ ግብጠባቂው አቤል ማሞ አዳነበት እንጂ ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።
በመጨረሻም ከረዥም ጊዜ ጉዳት በኃላ ዓምና በፕሪሚየር ሊጉ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ይፎካከር የነበረው ምንይሉ ወንድሙ ተቀይሮ ከገባ በኃላ መከላካዮች ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም በጠንካራ መከላከል ጎላቸውን ሲጠብቁ የዋሉት ነቀምቴዎች እድል ሳይሰጡ በመቅረታቸው ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሀምበሪቾ 2-0 ጅማ አባ ቡና
(አምሀ ተስፋዬ)
ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ከራሳቸው የግብ ክልል በመጀመር መስርተው ለመውጣት የሚጥሩት ሀምበሪቾዎች ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ገና በጊዜ ነበር። በአንደኛው ደቂቃ ላይ መቆያ አልታዬ ያቀበለውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ አክርሮ መቶ የግቡን ቀኝ አግዳሚ ታካ በመውጣት የተጋጣሚያቸውን ግብ ክልል በግዜ መፈተሽ የጀመሩት ሀምበሪቾች ወደ ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በ5ኛው ደቂቃ በአንድ ሀለት ቅብብል በቀላሉ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ደርሰው መሳይ አገኘሁ ያቀበለውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ ተረጋግቶ የግብ ጠባቂውን አቋቋም በመመልከት ለቡድኑ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል።
ከግቡ መቆጠር ባኋላ በሰከንዶች ልዩነት መሳይ አገኘሁ ከአላዛር አድማሱ የተሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠር ቢቃረብም የጅማ አባቡና ግብ ጠባቂ እንደምንም መልሶታል። ባለሜዳዎቹ ጥቃታቸውን በመቀጠል በኩል መሳይ አገኘው፣ ዳግም በቀለ እና ብርሀኑ አዳሙ በመጀመሪያው አጋማሽ ለግብ የቀረበ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን በአላዛር አድማሱ እና መቆያ አልታዬ አማካኝነት ከቀኝ እና ከግራ መስመር በሚጣሉት ኳሶች ጫና ማድረግም ችለው ነበር። በዚህም በ35ኛው ደቂቃ መሳይ አገኘው ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳግም በቀለ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
በዚህ አጋማሽ ጅማ አባ ቡናዎች ደካማ ጊዜ ያሳለፉ ሲሆን ኳስ መስርተው ለመጫወት የሚደርጉት ጥረት የሜዳው የመሀለኛው ክፍል ላይ ሲደርሱ ሲቋረጡ ተስተውሏል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀዝቀዛ እንቅስቃሴ ያስመለከተው ሁለተኛው አጋማሽ ሙከራ ለማስተናገድ ግን ደቂቃ አልፈጀበትም። በ46ኛው ደቂቃ ተደራጅተው ወደ ጅማ አባቡና የግብ ክልል የደረሱት ሀምበሪቾዎች በቴዲ ታደሰ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን ለረጅም ደቂቃዎች ሙከራ ያልታየ ሲሆን ጨዋታውም እጅጉን ተቀዛቅዞ ታይቷል። በ78ኛው ደቂቃ ላይ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ያመሩት ሀምበሪቾዎች በቢንያም ጌታቸው አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ሞክረው የነበረ ቢሆንም ሚኪያስ ጌታቸው አድኖታል።
ጅማ አባቡናዎች በእንቅስቃሴ ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው ቢገቡም የጠራ የግብ እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።
* በ72 ኛው ደቂቃ ላይ የአምበሪቾ አላዛር አድማሱ ጉዳት ደርሶበት በነበረበት ወቅት ጉዳቱን በመመልከት የጅማ አባ ቡናው ወጌሻ ቀድሞ በመግባት የሙያ ግዴታውን በማስቀደም የተጋጣሚን ቡድንን ሲረዳ ተስተውሏል።
በሚዛን አማን ሁለገብ ስታዲየም የተደረገው የቤንች ማጂ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ ጨዋታ 1 አቻ ተጠናቋል። በ36ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ አምበሉ ጌታሁን ገላዬ በግንባሩ ገጭቶ ቤንች ማጂን ቀዳሚ ሲያደርግ በ50ኛው ደቂቃ የቀድሞ ክለቡን የገጠመዉ ከማል አቶም በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎል ቀይሮ ሻሸመኔን አቻ አድርጓል። ከሻሸመኔ በኩል በ62ኛው ደቂቃ አንድ ተጫዋች በቀይ ወጥቷል።
ጨንቻ ላይ ጋሞ ጨንቻ ከአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ባለሜዳው ቡድን ከዕረፍት በፊት በስንታየሁ ዑታ አአ ከተማ ደግሞ በ77ኛው ደቂቃ ላይ አሥራት ሸገሬ የፍፁም ቅጣት ምት ጎሎችን አግኝተዋል።
ከሳምንቱ ተጣባቂ ጨዋታዎች መካከል የነበረው የሀላባ ከተማ እና ኢኮሥኮ ጨዋታ በሀላባ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ72ኛው ደቂቃ ላይ የበርበሬዎቹን ብቸኛ የማሸነፍያ ጎል ያስቀሰጠረው በኃይሉ ወገኔ ነው።
ከጨዋታው ሁለት ቀን በፊት የሀላባ ቡድን ለኢኮሥኮ የእንኳን ደህና መጣቹ አቀባበል እና እግርኳሱ የሰላም ተምሳሌት መሆን አለበት በሚል የእራት ፕሮግራም አዘጋጅተዋል። ኢኮሥኮዎች ለተደረገላቸው መልካም ነገርም ምስጋናቸውን በሶከር ኢትዮጽያ በኩል ገልፀዋል።
በዚሁ ምድብ ወላይታ ሶዶ ከተማ ከ ከፋ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሶዶ ላይ ባለው የፀጥታ ስጋት ሳይከናወን ቀርቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ