“ቡና የራሱ የሆነ ተጋጣሚን ሊቋቋምበት የሚችል አንድ ባህል እንዲያዳብር ነው ፍላጎቴ”- አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ በድህረ ጨዋታ ቃለምልልሳቸው ስለተቆጠሩት ግቦች፣ ስለ ውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች እና የክለቡ ደጋፊዎች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ስለዛሬው ጨዋታ

“በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለን ነበር፤ በሁለተኛው አጋማሽ ከነበረው ነገር አንፃር ይበልጥ መታረምና መሻሻል የሚኖርባቸው ነገሮች ስለመኖራቸው በግልፅ ተመልክተናል። በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ አሳልፈን ሰጥተናቸው ነበር። ስለዚህ እነዛ ስህተቶች መታረም አለባቸው ብዬ አስባለሁ።”

ስለ አራቱ ግቦች እና የባከኑ እድሎች

“በመጀመሪያ አጋማሽ ያገኘናቸው ጎሎች ጥሩ ናቸው ፤ የቡድኑን አካሄድ የጠበቁ ናቸው። በሁለተኛው አጋማሽ የተገኙት ግቦች ግን ጎሉ አካባቢ ከፍተኛ የተጫዋቾች ክምችት ነበር። ነገርግን የሄድንበት መንገድ ሁሌ የሚገኝ አይደለም፤ በጣም አስቸጋሪ ናቸው።”

“ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ስተደርስ ጫናዎች አሉ፤ ከደጋፊዎች ጫና ጀምሮ እስከ የተጋጣሚ ተጫዋቾች የሚሰጡት ትኩረት ጭምር እየጨመረ ነው የሚሄደው። ስለዚህ ወደዛ ክልል ስንገባ ትንሽ መረጋጋቶች ያስፈልጉናል። አንዳንዶቹ ሁኔታውን ረጋ ብሎ ካለማስተዋል የሚመጡ ናቸው። ስለዚህ ልጆቻችን በተወሰነ መልኩ መረጋጋት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ሲገቡ የሚረጋጉ ተጫዋቾች ግቦችን በቀላሉ ነው የሚያስቆጥሩት ይህንን ተጫዋቾቻችን ማዳበር ይኖርባቸዋል።”

ስለ ቡድኑ ደጋፊዎች

“ቡና የራሱ የሆነ አንድ ተጋጣሚን ሊቋቋምበት የሚችል አንድ ባህል እንዲያዳብር ነው ፍላጎቴ። በዚህ ውስጥ ነገሩ ታይቶ የሚጠቅም ከሆነ ይቀጥላል፤ የማይጠቅም ከሆነ ደግሞ ይቀራል። ስለዚህ በዋነኝነት ደጋፊው እዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ቢያደርግ መልካም ነው። ያለበለዚያ ሁልጊዜ ዝም ብሎ በሚሽከረከር ነገር ውስጥ ነው የምንሆነው። ስለሁልጊዜ ድጋፋቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ።”

ስለውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎች

“በሊጉ አብዛኞቹ ግብጠባቂዎች ከውጭ የመጡ ናቸው። የኛም ሆነ በተለይ የውጭ ሀገር የሚመጡት ግብጠባቂዎች በእጅ አጠቃቀም ረገድ ጥሩ ናቸው፤ እነሱን እንደ ተጫዋች ጨምረህ ለመጫወት በእግር አጠቃቀም ላይ እውነት ለመናገር እኔ ብዙዎቹ የውጭ ግብጠባቂዎች ላይ ጥሩ ነገር አላየሁም። ስለዚህ እኛ መጫወት ከምንፈልገው ነገር አንፃር የውጭ ግብ ጠባቂዎችን በማየት ምንም የሚያጓጓና የእኛ በሆኑ የሚያስብል ነገር ነገር የለም። ክለቦች የውጭ ተጫዋቾችን መጠቀም ቢኖርባቸው እንኳን የሚመጡት ተጫዋቾች ለእኛ ተጫዋቾች ሞዴል መሆን የሚችሉ መሆን መቻል አለባቸው። ነገ የእኛ ህፃናት ሲያድጉ ያንን ነገር ማድረግ የሚችሉ መሆን አለበት። አለበለዚያ የመጨረሻ የሀገራችንን እግርኳስ አዘእቅት ውስጥ የሚከተው ጉዳይ ይህ ነው። የውጭ ተጫዋቾች መምጣታቸው በእራሱ ችግር የለውም፤ ግን የሚያሳዩት ነገር የእኛ ታዳጊዎችን አቅም ግምት ውስጥ ያለከተተ ከሆነ በጣም ወደ መጨረሻ አዘእቅት የሚከተው ይህ ነው ብዬ ነው የማስበው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ