ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሴናፍ ዋቁማ ደምቃ ስትውል አዳማ እና ድሬዳዋ በሜዳቸው አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 3ኛው ሳምንት ጨዋታ ዛሬ በሁለት ጨዋታዎች ሲጀመር አዳማ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 6ለ0 ሲረመርም ድሬዳዋም ሀዋሳን በተመሳሳይ በሜዳው 3ለ1 ረቷል፡፡

አዳማ ላይ አዳማ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ በፍፁም የጨዋታ ብልጫ 6ለ0 አሸንፏል፡፡ የአዳማ ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጎልቶ ሊታይ በቻለበት በዚህ ጨዋታ ገና በጊዜ ነው ግብ መታየት የጀመረ ሲሆን 4ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ የፈጠረችላትን መልካም አጋጣሚ ሴናፍ ዋቁማ አስቆጥራ ቡድኗን በጊዜ ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ በ10ኛው ደቂቃ ላይም ሴናፍ ዋቁማ ከቅጣት ምት ግብ አስቆጥራ የግብ መጠኑን ወደ ሁለት አሳድጋለች፡፡

ጨዋታው ቀጥሎ 29ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር አጥቂዋ ሰርካዲስ ጉታ ሶስተኛ የቡድኑን ግብ ስታስቆጥር ሴናፍ ዋቁማ ደግሞ 33ኛው ደቂቃ ላይ ለቡድኗ አራተኛ ለራሷ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ግብ በማስቆጠር ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጫናዎችን እንደ አዲስ በተገነባው የአሰልጣኝ ሙለጎጃም እንዳለ ቡድን ላይ ሲያሳድር የነበረው የሊጉ መሪ በሰናይት ቦጋለ እና ሴናፍ ዋቁማ ተጨማሪ ግቦች በማስቆጠር ጨዋታው 6ለ0 በሆነ ውጤት ተደምድሟል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ በ7 ነጥቦች ሊጉ መምራት ሲጀምር ሴናፍ ዋቁማ ደግሞ በ5 ጎሎች የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱ ደረጃ አናት ላይ ተቀምጣለች።

ድሬዳዋ ላይ በተመሳሳይ 9:00 ድሬዳዋ ከተማን ከሀዋሳ ያገናኘው ጨዋታ በብርቱካናማዎቹ 3-1 አሸናፊነት ተደምድሟል። ለሀዋሳ ከተማ ሶስተኛ የሊጉ ጨዋታ ለድሬዳዋ ደግሞ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው ባለፈው ሳምንት ደግሞ አራፊ በመሆን ካሳለፉ በኃላ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ አድርገዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት እና የሀዋሳ ከተማዎች የመከላከል ስህተት በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ ሥራ ይርዳው 20ኛው ደቂቃ ድሬዳዋን መሪ ስታደግ 27ኛው ደቂቃ ላይ ነፃነት መና ሀዋሳን አቻ አድርጋለች።

ከእረፍት መልስ 72ኛው ደቂቃ ላይ ሥራ ይርዳው ተጨማሪ ግብ አክላ ድሬዳዋን ወደ 2ለ1 መሪነት ስታሸጋግር በ90+2ኛው ደቂቃ ታደለች አብርሀም ሦስተኛ ግብ አክላ በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ