ፍቅሩ ተፈራ ወደ ባንግላዴሽ ሊያመራ ከጫፍ ደርሷል

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ወደ ባንግላዴሽ ሊግ ሊያቀና እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ፍቅሩ በባንግላዲሽ ፕሪምየር ሊግ ለሚወዳደረው ሼክ ሩሰል ክሪራ ቻካራ ለመፈረም ከጫፍ ደርሷል፡፡ ተጫዋቹ እግር ኳስን በኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፊንላንድ፣ ህንድ እና ቬትናም በሚገኙ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን አሁን ደግሞ በሚያስገርም መልኩ የህንድ ጎረቤት ወደ ሆነቸው ባንግላዲሽ ለማቅናት መስማማቱን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ 

የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግን ከቼናይ ጋር ሻምፒዮን የሆነው ፍቅሩ በታህሳስ ወር ሊጉ ከተጠናቀቀ በኃላ ክለብ እየፈለገ ነበር፡፡ በውድድር ዓመቱ አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ፍቅሩ ወደ ደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪምየርሺፕ ይመለሳል የሚል ሰፊ ግምት የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻም ማረፊያውን የባንግላዴሽ መዲና ክለብ ወደ ሆነው ሼክ ሩሰል ክሪራ ቻካራ ሆኗል፡፡ ዝውውሩን ለመጨረስም ወደ ዳሃካ በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ወይም ዓርብ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግን የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረው ፍቅሩ ከ2012 በኃላ ሼክ ሩሰል ክሪራ ቻካራ ሰባተኛ ክለቡ ነው፡፡

ሼክ ሩሰል ክሪራ ቻካራ የመዲናዋ ዳሃካ ክለብ ሲሆን የ2014/15 የባንግላዴሽ ፕሪምየር ሊግን በሁለተኝነት አጠናቅቋል፡፡ በ2012/13 የሊጉ እና የፌድሬሽን ዋንጫ ሻምፒዮን ነበር፡፡ ክለቡ የሜዳ ጨዋታው 36ሺህ ተመልካች በሚይዘው የባንጋባብዱ ናሽናል ስታዲየም ላይ ያደርጋል፡፡ የባንግላዴሽ ፕሪምየር ሊግ 11 ክለቦች ሲሳተፉበት የተጀመረው ከ9 ዓመት በፊት ነው፡፡ ሊጉን ብዙ ግዜ በማንሳት ባለሪከርድ ክለብ አራት ግዜ የሊጉ ሻምፒዮን የሆነው ዳሃካ አባሃኒ ነው፡፡

ፍቅሩ ከዚህ ቀደም ለአዳማ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኦርላንዶ ፓይሬትስ፣ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ፣ ፍሪ ስቴት ስታርስ፣ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ፣ ቤድቬስት ዊትስ፣ ሜላኖ ዩናይትድ፣ አትሌቲኮ ኮልካታ፣ ቼናይ፣ታን ሆ፣ ኤፍ ኬ ማልዳ ቦልስላቭ እና ኬዩ ፓሎሱራ ተጫውቷል፡፡

ያጋሩ