ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነዋል። በስምንቱ ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ 11 ተጫዋቾችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች በየጨዋታዎቹ ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው።

አሰላለፍ፡ 4-4-3


ግብ ጠባቂ

ሰዒድ ሀብታሙ – ጅማ አባ ጅፋር

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከከፍተኛ ሊጉ አርባምንጭ ከተማ በሶስተኛ ተመራጭ ግብጠባቂነት ጅማን የተቀላበለው ሰዒድ በወረቀት ጉዳዮች እና በጉዳት ምክንያት ሌሎች ግብ ጠባቂዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ በሊጉ ቡድኑ ያደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል። ግብጠባቂው የተሰጠውን እድልም በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀመበት ይገኛል። ጅማ ከሜዳው ውጪ ከወልዋሎ ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለ ጎል አቻ ሲለያይ ድንቅ አቋሙን በማሳየትም ቡድኑን ታድጓል።

ተከላካዮች

አዳማ ማሳላቺ – ስሑል ሽረ

ስሑል ሽረ በፍፁም መከላከል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያለግብ በተለያየበት ጨዋታ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀትን በመምራት እንዲሁም በአንድ ለአንድ ግንኙነት ሆነ ወሳኝ የማጥቃት ሂደቶችን በማቋረጥ ረገድ ለቡድኑ ከፍተኛ ሚናን ተወጥቷል። ተጫዋቹ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተደረገው ጨዋታ በመሐል ተከላካይነት ቢሰለፍም በሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ በቀኝ መስመር ተከላካይነት አካተነዋል።

አሌክስ ተሰማ – መቐለ 70 እንደርታ

መቐለዎች የሲዳማ ቡናን በሜዳው ያለመሸነፍ ጉዞን በገታበት ጨዋታ ዳግም ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት የተመለሰው አሌክስ ተሰማ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ መሪነቱን ማስጠበቅ ላይ ያተኮረውን ቡድን ከኋላ በመምራት ፈጣኖቹ የሲዳማ ቡና አጥቂዎችን እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ እጅግ የተዋጣለት ነበር።

ከድር ኩሊባሊ – ፋሲል ከነማ

ፋሲል በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕናን በረታበት ጨዋታ ዋንኛ አጣማሪው ያሬድ ባየህ ባልነበረበት ያለ ቦታው ከተሰለፈው ሰዒድ ሁሴን ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የሆሳዕናዎችን ጥቃት በማክሸፍም ሆነ የቡድኑን የተከላካይ ስፍራ በመምራት ረገድ ውጤታማ ነበር።

ኃይለሚካኤል አደፍርስ – ሰበታ ከተማ

በሂደት ወደ የመጀመርያ 11 ቦታውን ያስጠበቀው ኃይለሚካኤል በተቃራኒው መስመር በማጥቃቱ ላይ የሚያተኩረው ጌቱ ኃ/ማርያም ይበልጥ በነፃነት እንዲያጠቃ በመፍቀድ ከተቀሩት ሁለት የመሀል ተከላካዮች በቅርበት እገዛ በመስጠት ውጤታማ ነበር።

አማካዮች

ነፃነት ገ/መድህን – ስሑል ሽረ

ሽረ ወሳኝ ተጫዋቾች ሳይዝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ነጥብ ባገኘበት ጨዋታ ለተከላካዮች እጅጉን ቀርቦ ሲያስፈልግም እንደ ሶስተኛ የመሐል ተከላካይ በመሆን ቡድኑ ለተከተለው የመከላከል አቀራረብ ተለዋዋጭ ሚናን በመወጣት ጥሩ ግልጋሎት አበርክቷል።

ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ

በክረምቱ ባህርዳር ከተማን ከተቀላቀለ ወዲህ በመስመሮች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ለነበረው የባህርዳር ከተማ ሌላ የማጥቃት አማራጭን እየሰጠ ይገኛል። መሐል ለመሐል ለሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጥሩ የኳስ አቅርቦት አማራጭ ከመሆን በዘለለ በዚህ ሳምንትም ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ለሁለኛ ጊዜም የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት ችሏል።

ኢድሪስ ሰዒድ – ወላይታ ድቻ

ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ በመምታት አዳማ ላይ ካስቆጠራት ግሩም ግብ በተጨማሪ በባዬ ገዛኸኝ ፍጥነት ላይ ለተመሠረተው የወላይታ ድቻ የማጥቃት እንቅስቃሴ ኳሶችን ከተከላካዮች እየተቀበለ በማድረስ በኩል በጣም ውጤታማ ነበር። ድቻን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ ዓመቱ በሊጉ ጥሩ ጅማሮን እያደረገ የሚገኘው አማካዩ በጉዳት በርካታ አማካዮቹን በጨዋታው ላይ ያላሰለፈው ቡድን ዋነኛ ተጫዋች ነበር።

አጥቂዎች

እንዳለ ደባልቄ – ኢትዮጵያ ቡና

ከፍ ባለ የራስ መተማመን ስሜት የሚንቀሳቀሰው እንደለ ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳን ሲረታ አንድ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ሁለቱ በጨዋታ እንቅስቃሴ ያስቆጠራቸው ግቦች በ4 ግቦች ከፋሲሉ ሙጂብ ቃሲም ጋር የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን ሰንጠረዡን እንዲመራ አስችሎታል። ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ ከቡድኑ እንቅስቃሴ ጋር እየተዋሀደ መሆኑንም አሳይቷል።

ማማዱ ሲዲቤ – ባህርዳር ከተማ

ከአማካዩ ፍፁም ዓለሙ ጋር ጥሩ ተግባባቶን የፈጠረው ግዙፉ ማሊያዊ አጥቂ ማማዱ ሲዴቤ ድሬዳዋን ሲረቱ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር አንድ ኳስ ማመቻቸት ችሏል። ቡድኑ በመስመርም ሆነ መሐል ለመሀል ጥቃት እንዲሰነዝር የአጥቂው የቦታ አያያዝ እና ያለኳስ እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

አማኑኤል ገ/ሚካኤል – መቐለ 70 እንደርታ

መቐለ ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ድል ሲቀናው የዐምናው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አማኑኤል እንደሌሎች ጊዜያት ሁሉ ልዩነት ፈጣሪ ነበር። በጨዋታው ውስን የግብ አጋጣሚ ላገኙት መቐለዎች አንድ ግብ ከማስቆጠሩም አልፎ ሌላኛው የቡድን አጋሩ ያሬድ ከበደ ላስቆጠራት ግብ በማመቻቸትም ለቡድኑ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስገኝቷል።

ተጠባባቂዎች

በሳምንቱ የሶከር ኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ ሊካተቱ ከሚገባቸው ተጫዋቾች መካከል ምንም እንኳ አንድ በጨዋታ፣ አንድ በፍ/ቅ/ም ጎል ቢያስናግድም ጥሩ ጥሩ የጎል አጋጣሚዎችን ሲያመክን የተስዋለው የወላይታ ድቻው መኳንንት አሸናፊ ግብ ጠባቂነት የሚጠቀስ ነው።

ለምርጫ አስቸጋሪ በነበረውና በርካታ ተጫዋቾች ጥሩ አቋም ባሳዩበት የተከላካይ ሥፍራ ላይ ቡድኖቻቸው ከሜዳ ውጪ ጎል ሳይቆጠርባቸው እንዲመለሱ ወሳኝ ሚና የተወጡት የሰበታ ከተማው ዩጋንዳዊ ተከላካይ ሳቪዮ ካቩጎ እና የጅማ አባ ጅፋሩ መላኩ ወልዴ በተጠባባቂነት ተካተዋል።

አማካይ ሥፍራ ላይ ምንም እንኳ ቡድኑ ሽንፈት ቢያስተናግድም በእረፍት ሰዓት ተቀይሮ በመግባት ጥሩ የተንቀሳቀሰው ብርሀኑ አሻሞ ሲካተት በመስመር በኩል ጥሩ ጊዜ ያሳለፉትና ቡድኖቻቸው የዓመቱን የመጀመርያ ድል እንዲያሳካ የረዱት የሰበታው አስቻለው ግርማ እና የኢትዮጵያ ቡናው አቤል ከበደ ተካተዋል።

አጥቂ ስፍራ በተከታታይ ጨዋታዎች ጥሩ አቋም እያሳየ የመጣውና በሳምንቱ ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው የአዳማ ከተማው ዳዋ ሆቴሳ በተጠባባቂዎች ከተካተቱት መሐል ነው።

:copyright: ሶከር ኢትዮጵያ