በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ3ኛው ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂደው አቃቂ ቃሊቲ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ቀንቷቸዋል።
09:00 የጀመረው የአቃቂ ቃሊቲ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በባለ ሜዳዎቹ አቃቂዎች 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። አጀማመራቸው ያላማረው ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢያስመለክቱንም ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ባለሜዳዎቹ አቃቂዎች ነበሩ። 11ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ፀባኦት መሐመድ በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት አቃቂዎችን ቀዳሚ አድርጋለች።
አርባምንጮች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በመሐል ሜዳ የእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም ወደ ማጥቃት ሽግግሩ ላይ የነበራቸው ድክመት የጎል እድል ለመፍጠር እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል። የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቆጣጠር በፍጥነት ኳሶችን ወደ ፊት ለአጥቂዎች በመጣል ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት አቃቂዎች በአንፃሩ የተከተሉት አጨዋወት ረድቷቸው በ31ኛው ደቂቃ ሰላማዊት ኃይሌ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ባስቆጠረችው ጎል ልዩነቱን አስፍተዋል።
ሁለተኛ ጎል ሲቆጠርባቸው የተቀዛቀዙት አርባምንጮች 41ኛው ደቂቃ እነርሱ በፈጠሩት ስህተት ሰላማዊት ኃይሌ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራ በአቃቂ ቃሊቲ 3-0 መሪነት ለእረፍት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል በ52ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል የተመታውን የአቃቂዋ ግብጠባቂ ሺብሬ ካንኮ ስትተፋው የትምወርቅ አሸናፊ አግኝታ አስቆጥራለች። አቃቂዎች አስቀድመው በሦስት ጎል ልዩነት መምራታቸው ያዘናጋቸው ሲሆን በ74ኛው ደቂቃም በአርባምንጭ በኩል ተቀይራ በገባችው መቅደስ ከበደ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል።
በቀረው ደቂቃ አርባምንጮች ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ይሄዳሉ ቢባልም አቃቂዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጠንካራ መከላከል ሰምሮላቸው ጨዋታው በአቃቂ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አዳጊው አቃቂ ቃሊቲ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል።
11:00 የቀጠለው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ንግድ ባንክ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር አሰመልክቶን በንግድ ባንክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የኤሌክትሪክ አሰልጣኝ መሠረት ማኒ ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን ይዛ ብትቀርብም ወደ ጎል በሚደርሱበት ወቅት አጥቂዎቹ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በክፍት ጨዋታ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም። ይሁን እንጂ በቆመ ኳስ በአዳነች ጌታቸው አማካኝነት እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። በእንቅስቃሴ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ልምድ እንዳለው ቡድን የኤሌክትሪክን አጨዋወት በመቆጣጠር በሽታዬ ሲሳይ አማካኝነት አደጋ ሲፈጥሩ የቆዩት ንግድ ባንኮች በ19ኛው ደቂቃ ከመዓዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ሕይወት ደንጊሶ በግንባሯ በመግጨት የጨዋታውን ብቸኛ የማሸነፊያ ጎል አስቆጥራለች።
የአንድ ጎል ብልጫ ያላስተማመናቸው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የመስመር ተጫዋቾቹ ብርቱካን ገ/ክስቶስ እና ታሪኳ ደቢሶን በመቀየር ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም ትርጉም ያለው የጎል ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። በአንፃሩ ኤሌክትሪኮች በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ከአማካይ ኳስ ተቀብሎ ወደ ጎልነት መቀይ የሚችል ሁነኛ አጥቂ ባለመኖሩ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታው በንግድ ባንክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ተከታታይ ጨዋታውን ሲያሸንፍ በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል።
የሊጉ 3ኛ ሳምንት ነገ ሲጠናቀቅ ዲላ ላይ ጌዴኦ ዲላ ከ መቐለ 70 እንደርታ ይጫወታሉ።