የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና ተደርገዋል። ወልዋሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጥብ ሲጥል ሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል አሳክተዋል። በሳምንቱ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ላይ የተመለከትናቸው ነጥቦችንም በቀጣይ መልኩ ለመቃኘት ሞክረናል።
1. ክለብ ትኩረት
*የሲዳማ ቡና በሜዳው ያለመሸነፍ ጉዞ መገታት
ላለፉት ዓመታት በሊጉ በጠንካራ ተፎካካሪነት መዝለቅ የቻለው ሲዳማ ቡና በተለይ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን እስከ መጨረሻ ሳምንት በዘለቀው የዋንጫ ፉክክር ላይ ብርቱ ትንቅንቅ ሲያደርግ ቆይቶ በስተመጨረሻ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል።
ከዚህ አስደናቂ ግስጋሴ ጀርባ ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ማለትም የመጫወቻ ሜዳውን ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ ከቀየረ በኋላ በሀዋሳ ስታዲየም ላይ በበርካታ ደጋፊዎቹ ታግዞ ለተጋጣሚዎች እጅግ ፈተና ሲሆን ተስተውሏል። በሀዋሳ ስታዲየም ባደረጋቸው 19 ጨዋታዎች ሳይሸነፍ የዘለቀው የሲዳማ ቡና ጉዞ ባሳለፍነው ቅዳሜ በመቐለ 70 እንደርታ ባስተናገዱት የ2ለ1 ሽንፈት ሊገታ ችሏል።
*የሰበታ ከተማ የመጀመርያ ሦስት ነጥብ
ወደ ሊጉ አዲስ ካደጉ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሰበታ ከተማ በስተመጨረሻም በ4ኛ ሳምንት በአቢዮ አርኤርሳሞ ስታዲየም ወልቂጤ ከተማን 1ለ0 በመርታት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ማሳካት ችሏል። ሦስት ነጥቡ እጅግ ያስፈልጋቸው የነበሩት ሰበታዎች በ8ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ ካስቆጠራት ግብ በኋላ ጥንቃቄን በመምረጥ የተገኘችውን የጎል ልዩነት በጥሩ መከላከል አስጠብቀው ሊወጡ ችለዋል።
*ሀዲያ ሆሳዕና እና የዲሲፕሊን ግድፈት
በ4ኛ ሳምንት በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም በፋሲል ከተማ 3ለ0 በተሸነፈበት ጨዋታ አካላዊ ንኪኪዎች በርከት ብሎ ተስተውሏል። ውጥረት በተሞላው ጨዋታ የሆሳዕና ተጫዋቾች እያንዳንዱን የዳኛ ውሳኔ ለመቀበል በማንገራገር የእለቱ ዳኛን ሲከቡና ሲያዋክቡ በስፋት ተስተውሏል። የመስመር ተከላካያቸው ሱራፌል ዳንኤልን በቀይ ካርድ ያጡት ሆሳዕናዎች 8 ቢጫ ካርዶች የተመለከቱ ሲሆን አመዛኙ የማስጠንቀቂያ ካርድ ምክንያት በተደጋጋሚ ከዳኛ ጋር ሲፈጥሩ የነበረው ሰጣ ገባ ነው።
አንዴ የተወሰነ የዳኛ ውሳኔ በማይሻርበት ሁኔታ ተጫዋቾችም ሆነ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ከስፖርቱ መርህ ውጭ በመሆን በዚህ መልኩ ደጋፊን ለስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት የሚያነሳሳ ተግባር መፈፀማቸው ራስን ለቅጣት ከመጋበዝ በዘለለ ለቡድኑ የሚፈይደው አንዳች ነገር ባለመኖሩ የክለቡ ተጫዋቾች ከመሰል ድርጊቶች ሊቆጠቡ ይገባል።
*እየተሻሻለ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና
ዘንድሮ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስር ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ከዚህ ቀደም ይነሳበት የነበረውን ወደ ተጋጣሚ የአደጋ ክልሎች የማይደርስ የተገደበ የኳስ ቅብብልሽ አሁን እየተሻሻለ እየመጣ ይገኛል። በሁለተኛ ሳምንት ከጅማ አባ ጅፋር ከተደረገው ጨዋታ ጀምሮ ወደፊት በመድረስ በተደጋጋሚ የግብ እድሎችን እየፈጠሩ የሚገኙ ሲሆን በዕለተ እሁድም ሀዋሳ ከተማን 4-1 መርታት ችለዋል።
አሰልጣኙ ከጅማው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ዋነኛው ነገር የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር መቻሉ መሆኑንና ሌሎች ነገሮች በሂደት እንደሚታረም በገለፁት መሠረት ቡድኑ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ከጥሩ እንቅስቃሴ ጋር ግቦችንም ማስቆጠር ጀምሯል።
*ስሑል ሽረ እና አሉታዊ አቀራረባቸው
አራት የቡድኑን ወሳኝ ተጫዋቾችን ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ሳያካትቱ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠሙት ሽረዎች በፍፁም የመከላከል አቀራረብ አንድ ነጥብ ተጋርተው ለመመለስ በቅተዋል።
መከላከል እንደ አንድ የጨዋታ ስልትነቱ አለመሸነፍን ተቀዳሚ አማራጭ አድርጎ በማሰብ ለመከላከል ወደ ጨዋታ መግባት በራሱ ችግር የለውም። ነገርግን ለ90 ደቂቃ መከላከል ያሰበ አንድ ቡድን ይህን ሂደት እንዴት መተግበር አለበት በሚለው ዙሪያ በሀገራችን ክለቦች ላይ የአረዳድ ስህተቶች ያሉ ይመስላል።
ቡድኖቻችን ጎል ላለማስተናገድ ሲያስቡ የተዋሀደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ላይ አተኩሮ ከመስራት ይልቅ የተጋጣሚ ክለብ ደጋፊዎችን በሚያነሳሳ መልኩ ገና ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ ሰዓት በመግደል መድረሻቸው ባልታወቁ ረጃጅም ኳሶች ኳስን ከአካባቢ ማራቅና መሰል ድርጊቶች ሲፈፀሙ ይስተዋላል። የሽረው ግብጠባቂም ገና ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ ‘ተጎድቻለሁ’ በሚል ሰበብ በተደጋጋሚ ሰዓት ሲገድል፣ የመልስ ምቶችን ለመምታት ዘለግ ያለጊዜ ሲወስድ ተስተውሏል። ይህን መሰል ድርጊቶች የጨዋታ ሂደት እየተገባደደ በሚገኝባቸው ደቂቃዎች ሲተገበሩ በእግርኳስ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ቢሆንም ይህ ሲሆን አልተመለከትንም።
የመከላከል አቀራረቦች የተወገዙ ባይሆኑም ቡድኖች በአተገባበሩ ላይ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ምክንያቱም መሰል የጊዜ ገደላ አካሂዶች ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩበት በሚገኘው የሀገራችን የስታዲየሞች ቀጣይ ሰላም ላይ ተግዳሮት መሆናቸው አይቀርም።
*ድሬዳዋ ከተማ እና ‘የሚያፈሰው’ የተከላካይ መስመር
በሊጉ አስቸጋሪ ጊዜያትን እያሳለፉ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁንም ግቦችን ማስተናገዳቸውን ቀጥለዋል።
በአንድ ሳምንት ልዩነት በባህር ዳር ከተማ እና በፋሲል በድምሩ በሁለት ጨዋታዎች 9 ግቦችን ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች በመከላከሉ ረገድ መሻሻል የሚገባቸው ክፍተቶች ስለመኖራቸው የሚታይ ሀቅ ነው። ምንም እንኳን የመከላከል ስራ በተናጥል ለተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ብቻ የሚሰጥ ባይሆንም ቡድን አጠቃላይ የመከላከል አወቃቀሩን መፈተሽ ይኖርበታል።
2. ተጫዋቾች ትኩረት
* ባለ ሐት-ትሪኩ እንዳለ ደባልቄ
ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳን 4ለ1 በረታበት ጨዋታ እንዳለ ደባልቄ መድመቅ ችሏል።
ከሰሞኑ የተገኙ የግብ አጋጣሚዎችን እየተጠቀመ አይደለም በሚል ከደጋፊዎች ተቃውሞ እያስተናገደ የነበረው እንዳለ ባሳለፍነው ሳምንት ቡድኑ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር 1-1 ሲለያዩ የቡናን በውድድር ዘመኑ የሊጉ የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን እሁድ ደግሞ ሐት-ትሪክ በመስራት በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ደረጃ ሙጂብ ቃሲምን መስተካከል ችሏል።
ከፍ ባለ የራስ መተማመን ስሜት የሚንቀሳቀሰው እንዳለ በጨዋታው አንድ በፍፁም ቅጣት እንዲሁም ሁለቱ በጨዋታ እንቅስቃሴ ያስቆጠራቸው ግቦች ይህንኑ የሚያሳዩ ነበሩ።
* የፍፁም ዓለሙና ማማዱ ሲዲቤው አዲሱ ባህር ዳር
አየዐምና በሊጉ በተካፈሉበት የመጀመሪያ ዓመት አስደናቂ አጀማመር ማድረግ የቻሉትና በሂደት ተዳክመው የተስተዋሉት ባህር ዳሮች በተለይ በማጥቃቱና ግቦችን በማስቆጠር ረገዶች ክፍተቶች ነበሩባቸው።
ዘንድሮ በአዲስ መልኩ ቡድኑን የተረከው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ክፍተቱን ለመድፈን ጥሩ ዝውውሮችን ፈፅሟል ለማለት በሚያስችል መልኩ በተለይ ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በርከት ያሉ ግቦችን ማስቆጠር ጀምሯል።
ከአምናው በተሻሉ በሜዳቸው ብዙ ግቦች እያስቆጠሩ የሚገኙት ባህርዳሮች በሊጉ በሜዳው ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ብቻ 7 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። ከእነዚህም ውስጥ አማካዩ ፍፁም ዓለሙ እና አጥቂው ማማዱ ሲዲቤ እያንዳንዳቸው ሦስት ግቦችን በማስቆጠር በፋሲል ተካልኝ እየተገነባ ለሚገኘው ባህር ዳር ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ አይነተኛ መሳሪያ እየሆኑ መጥተዋል።
* ሁለገቦቹ የወልዋሎ ተጫዋቾች
በዚህ ሳምንት የዓመቱ የመጀመሪያ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ወልዋሎዎች አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እንደወትሮው ሁሉ አሁንም የተጫዋቾቻቸውን ሚና መለዋወጣቸውን ቀጥለዋል።
በዚህ ሳምንት ደግሞ ከዚህ ቀደም በመስመር ተከላካይነት የምናውቀው እንዲሁም ዘንድሮ በመሀል ሜዳ ተጫዋቾችነት ሲሰለፍ የነበረው ገናናው ረጋሳ በቅዳሜው ጨዋታ በመሐል ተከላካይነትና ሲጀምር በተመሳሳይ አማካዩ ስምኦን ማሩ በመሀል ተከላካይነት ተሰልፎ የተመለከትን ሲሆን የመስመር ተከላካዩ ሄኖክ መርሹ እና አጥቂው ኢታሙና ኬይሙኒ በአማካይነት ተሰልፈው ለመመልከት ችለናል።
አሰልጣኙ በዚህ ጉዳይ ላይ ባለፈው ሳምንት በሰጡት አስተያየት ከግብ ጠባቂ ውጭ ተጫዋቾችን የሚያስፈርሙት ሁለገብ ሚናን እንዲወጡ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
3. የጳውሎስ ጌታቸው ተመሳሳይ ድህረ ጨዋታ አስተያየት
ጅማ አባ ጅፋርን በክረምቱ የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ቡድኑን በአዲስ መልኩ ገንብተው ለአዲሱ የውድድር ዘመን ቀርበዋል።
ከሜዳ ውጭ ባሉ ውጥንቅጦች የተተበተበው ቡድኑ ከተገመተው በተፃራሪ ተስፋ ሰጪ የውድድር ዘመን ጅማሮን ማድረግ ችሏል። እስካሁን ድረስ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ሽንፈት ሲያስተናግድ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ መጋራት ችሏል። ይህም እስካሁን በሜዳቸው ምንም ጨዋታ ካለማድረጋቸው ጋር ተዳምሮ ጥሩ የሚባል ውጤት ነው።
ነገርግን የቡድኑ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከአራቱም ጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ በሚሰጣቸው አስተያየቶች ላይ ሁሌም ተመሳሳይ ሀሳቦችን ሲሰጡ ይደመጣሉ፤ በድህረ ወልዋሎ ጨዋታ ላይ የሰጡትን ሀሳብም ለማሳያነት እናንሳ
“ቀጣይ ከወጣት ተጫዋቾቻችን ብዙ ጥሩ ነገር ታያላችሁ ፤ አራት ጨዋታዎችን አድርገን አራቱንም ከሜዳችን ውጭ ነው ያደረግነው። ተጫዋቾቹ ብዙ ልምድ የሌላቸው ናቸው፤ በአጠቃላይ ባመጣኋቸው ተጫዋቾች ደስተኛ ነኝ።”
አሰልጣኙ መሰል አስተያየቶችን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ሲሰጡ አድምጠናል። እውን አስተያየቱ በሜዳ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልፅ ነውን?
የቡድኑ የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች በአመዛኙ በሊጉ የመጫወት ልምድ ያላቸው ስለመሆኑ የቡድኑን የተጫዋቾች ዝርዝር መመልከት ብቻ በቂ ነው። ከዚህ አስተያየት ጀርባም በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ቡድኑ ውጤት ባለማስመዝገቡ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለማለዘብ የተዘየደ የህዝብ ግንኙነት ስትራቴጂ አልያም በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ቅቡልነትን ለመፍጠር የታቀደ ሀገር ሳይሆን እንደማይቀር መናገር ይቻላል።
4. የሀዋሳ ስታዲየም
የሀዋሳ ስታዲየም በተለይም ሲዳማ ቡና ጨዋታዎችን በሚያደርገሰበት ወቅት ማስተናገድ ከሚችለው ተመልካች በላይ በተመልካች ሲጨናነቅ መስተዋል ከጀመረ ሰነባብቷል። በዚህኛው ሳምንትም ሲዳማ ቡና መቐለ 70 እንደርታን ባስተናገደበት ጨዋታ ስታዲየሙ በጊዜ በመሙላቱና ከውጭ በርካታ ቁጥር ያላቸው የስፖርት ቤተሰብ ወደ ሜዳ በኃይል ለመግባት ባደረጉት ጥረት ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ እስከመተኮስ የደረሰ ትርምስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
መሰል የተመልካች ፍላጎትና የስታዲየሙ የመያዝ አቅቅም አለመጣጣም እክሎች ሲፈጠሩ ይህ የመጀመሪያ ባለመሆኑ ክለቡ በቀጣይ በእድሳት ላይ የሚገኘውን የሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ስራው በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ርብርብ በማድረግ ጨዋታዎች በግዙፉ ስታዲየም ሊከውንበት የሚችልበትን አማራጭ ማጤን ሳይኖርበት አይቀርም።
© ሶከር ኢትዮጵያ