የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንትን የምንዘጋው እንደተለመደው በሳምንቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች ይሆናል።
ጎል
– በአራተኛው ሳምንት በአጠቃላይ 21 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ከ3ኛ ሳምንት በ10 ጎሎች የላቀ ሲሆን ዓመቱ ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ ከሁለተኛው ሳምንት ቀጥሎ ከፍተኛው ነው።
– እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ በዚህ ሳምንትም ስድስት ጨዋታዎች ላይ ጎሎች ሲቆጠሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ስሑል ሽረ እንዲሁም ወልዋሎ ከ ጅማ አባ ጅፋር ያለ ጎል የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው።
– በዚህ ሳምንት የተቆጠሩት 21 ጎሎች በ16 የተለያዩ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። ከሁለተኛው ሳምንት (18) ቀጥሎ በርካታ ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር የተሳተፉበት ሆኖም አልፏል።
– ጎል ካስቆጠሩ 16 ተጫዋቾች መካከል 12 ጎሎች በመሐል አጥቂነት በተሰለፉ ተጫዋቾች ሲቆጠር 6 ጎሎች በአማካዮች፣ ሦስት ጎሎች ደግሞ በመስመር ተጫዋቾች አማካኝነት ተቆጥረዋል።
– እንዳለ ደባልቄ ሦስት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛውን የጎል ቁጥር ሲያስመዘግብ ማማዲየዱ ሲዲቤ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና ፍፁም ዓለሙ በሁለት ጎሎች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
– ከ21 ጎሎች መካከል 17 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ ቀሪዎቹ አራት ጎሎች በፍፁም ቅጣት ምት ተቆጥረዋል።
– ከዚህ ሳምንት ጎሎች መካከል 17ቱ በእግር ተመትተው የተቆጠሩ ናቸው። አራት ጎሎች ደግሞ በጭንቅላት ተገጭተው የተቆጠሩ ናቸው።
– ለተቆጠሩ ጎሎች አመቻችቶ በማቀበል ረገድ 12 ተጫዋቾች ተሳትፈዋል። ቀሪዎቹ በፍፁም ቅጣት ምት ወይም ከተቃራኒ ተጫዋቾች ተነጥቀው የተቆጠሩ ናቸው።
– ከ21 ጎሎች መካከል ሦስት ጎሎች ብቻ ከሳጥን ውጪ ተመትተው ሲቆጠሩ 18 ጎሎች የሳጥን ውስጥ ውጤቶች ናቸው።
– እስካሁን በሊጉ 32 ጨዋታዎች ሲደረጉ 67 ጎሎች ተቆጥረዋል። ወልዋሎ እና ፋሲል በ8 ጎሎች በርካታ ጎል ያስቆጠሩ ቡድኖች ሲሆኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር በ1 ጎል ዝቅተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ናቸው። ጊዮርጊስ (0 ጎል) ምንም ጎል ያልተቆጠረበት ሲሆን 11 ጎል ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ ከፍተኛ ጎል የተቆጠረበት ቡድን ሆኗል።
የሰበታ ከተማ ድል
– ሰበታ ከተማ ወልቂጤን 1-0 ያሸነፈበት ውጤት ከ8 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘ የሊግ ድል ነው። ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ያሸነፈው ሰኔ 19 ቀን 2003 ሲሆን ሐረር ቢራን 2-0 አሸንፎ ነበር።
ሲዳማ ቡና እና “ጉዞ ገቺው” መቐለ
– ሲዳማ ቡና በሜዳው የነበረው ያለመሸነፍ ጉዞ ከ21 ጨዋታ በኋላ በመቐለ 70 እንደርታ የ2-1 ሽንፈት ተገትቷል። ሲዳማ ቡና ሚያዚያ 9 ቀን 2010 በወቅቱ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ይርጋለም ላይ 3-1 ከተሸነፈ በኋላ በተከታታይ ባደረጋቸው 21 ጨዋታዎች 18 በማሸነፍ ሦስት ጊዜ ብቻ አቻ ተለያይቶ በመጨረሻም ለዐምናው ቻምፒዮን እጅ ሰጥቷል።
እውነታውን በግጥምጥሞሽ ስንመለከት ከሁለት ዓመት በፊት በጅማ ሽንፈት ሲያስተናግዱ ኦኪኪ አፎላቢ ጎል ያስቆጠረ ሲሆን በመቐለ ሲሸነፉ ደግሞ አጥቂው ለጎል አመቻችቶ አቀብሏል። በተጨማሪም በወቅቱ የጅማ አሰልጣኝ የነበሩት ገብረመድህን ኃይሌ ሲሆኑ አሁን ላይ መቐለ አሰልጣኝ የሆኑት በተመሳሳይ ገብመድህን ናቸው።
– መቐለ 70 እንደርታ ረዘም ያለ በሜዳ ያለመሸነፍ ሪከርድ ሲገታ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም። በ2010 የውድድር ዘመን ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የአዳማ ከተማ የ30 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞን 2-0 በማሸነፍ መግታቱ ይታወሳል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ
– ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም ጎል ሳይቆጠርበት ዘልቋል። ከአራት ሳምንታት በሦስቱ ያለ ጎል ሲለያይ አንዱን ጨዋታ 1-0 አሸንፏል። ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ጎል ያላስናገደው አዳማ በአንፃሩ በዚህ ሳምንት ሁለት ጎሎች አስተናግዷል።
የመጀመርያ…
– ኢትዮጵያ ቡና እና ሰበታ ከተማ የዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን አስመዝግበዋል።
ካርዶች
– ሳምንቱ በርካታ ቢጫ ካርድ የተመዘዘበት ሆኖ አልፏል። 37 ቢጫ እና ሁለት ቀይ (ሁለተኛ ቢጫ) ካርዶች የተመዘዙት ይህ ሳምንት በሁለተኛው ሳምንት ከተመዘገበው (35 ቢጫ ካርዶች) ብልጫ አስመዝግቧል።
– ከአጠቃላይ 39 ካርዶች መካከል 37 ለተጫዋቾች ሲመዘዝ ለአሰልጣኝ (የሽረው ሳምሶን አየለ) አንድ ተመዟል።
– በፋሲል ከነማ (1 ቢጫ) እና ሀዲያ ሆሳዕና (7 ቢጫ እና 1 ቀይ) መካከል የተደረገው ጨዋታ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበበት ሲሆን የሽረ (6 ቢጫ እና 1 ቀይ) እና የቅዱስ ጊዮርጊስ (0) ተከታዩን ደረጃ ይዟል። አንድ ቢጫ ብቻ የተመዘገበበት የወልዋሎ (0) እና ጅማ አባ ጅፋር (1) ዝቅተኛው ቢጫ ካርድ የተመዘገበበት ሆኖ አልፏል።
– በሊጉ እስካሁን በተደረጉ 32 ጨዋታዎች 103 ቢጫ እና 5 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ