‹‹ በሊዮፓርድስ ጨዋታ የፈጠርነው ስህተት እንዳይደገም ጥረት እናደርጋለን ›› አሰልጣን ገብረመድህን ኃይሌ

 

የ2007 የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው መከላከያ በ2016 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ይካፈላል፡፡ በቅድመ ማጣርያው የግብፁ ምስር አል ማቃሳን የሚገጥመው ጦሩ የመጀመርያ ጨዋታውን በመጪው ቅዳሜ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያደርጋል፡፡

በመከላከያ የልምምድ ሜዳ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ክለቡ ቅዳሜ የሚያደርገውን ጨዋታ አስመልክቶ ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡ እኛም ለእናንተ አንባብያን በሚመች መልኩ እነሆ ብለናል፡፡

IMG_1403

ስለ ተጋጣሚያቸው

‹‹ተጋጣሚያችን ማን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የነሱን የተወሰነ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪድዮም ተመልክቻለሁ፡፡ ምስር አል ማቃሳ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የግብፅ ቡድኖች እዚህ ሲመጡ የሚያደርጉትን ስለምናውቅ በቪድዮ ያየሁትን እዚህ ይተገብሩታል ብዬ አላስብም፡፡ ጨዋታውን በማቀዝቀዝ በሜዳቸው ለሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ሊጠቅማቸው የሚችል ውጤት ይዘው ነው መሄድ የሚፈልጉት፡፡

ትኩረት ያደረግነው ጨዋታውን በማፍጠን ውጤት ማምጣት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍጥነጥ ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህንንም ሰርተናል ብለን እናምናለን፡፡ በጉዳት  በኩልም ቢሆን ችግር የለብንም፡፡ ››

 

ስለ ጨዋታው

‹‹ ዘንድሮም እንደአጋጣሚ ሆኖ ጠንካራ ቡድን ነው የደረሰን፡፡ ጠንካራ መሆኑ ፈታኝ ቢሆንም በሌላ በኩል ጥሩ ጎንም አለው፡፡ ጨዋታው አቅማችንን እንድናይ ያደርገናል፡፡ ራሳችን ጋር ያለው ምን እንደሆነም ያሳያል፡፡ በየዙሩ ጠንካራ ቡድኖች ባገኘን ቁጥር ልምድ እንድናገኝ እና በየጨዋታው በራስ መተማመናችን እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡

ምስር አል ማቃሳ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አናሸንፍም ማለት አይደለም፡፡ በ2006 ካሸነፈን ሊዮፓርድ የቀሰምነው ልምድ አለ፡፡ ያኔ የፈጠርነው ስህተት እንዳይደገም ጥረት እናደርጋለን፡፡ ደካማ ጎናችንንም አውቀናል፡፡ ከዛ ውጪ ግን ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን አጥቅተን ለመጫወት ጥረት እናደርጋለን፡፡ አጥቂዎቼ ላይ ለውጥ አይቼባቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ በማጥቃት በኩል ጥሩ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ››

 

ድጋፍ

‹‹ የስፖርት አፍቃሪው ድጋፉን ከሰጠን የተሻለ ውጤት እናመጣለን፡፡ የህዝቡ ድጋፍ ትንሽ ቀዝቀዝ ያለ ነው፡፡ የሃገር ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ድጋፉን እንዲሰጠን ጥሪ አቀርባለሁ፡፡››

ያጋሩ