በጉዳት ከሜዳ የራቁት የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ወቅታዊ ሁኔታ…

በዳንኤል መስፍን እና ኤልያስ ኢብራሂም

የ2012 የውድድር ዓመት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ የተጫዋቾች ጉዳት እያስተናገዱ ከሚገኙ ክለቦች መካከል ፋሲል ከነማ አንዱ ነው። በዓመቱ መጀመርያ እና ባለፈው ዓመት ጉዳት ከደረሰባቸው ተጫዋቾች መካከል አቤል እያዩ፣ ኤፍሬም ክፍሌ እና መልካሙ ታውፈር ከጉዳታቸው ያገገሙ ሲሆን ለመጀመርያ ተሰላፊነት ከሚፎካከሩ ተጫዋቾች መካከል የሆኑት አብዱራህማን ሙባረክ፣ እንየው ካሣሁን እና ሰለሞን ሀብቴን ወቅታዊ ሁኔታን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ከስብስቡ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ጉዳት የራቀው አብዱረህማን ሙባረክ ነው። ግንቦት 17 ቀን 2011 ሶዶ ላይ ፋሲል ከነማ በወላይታ ድቻ በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ የጉልበት ጉዳት ያጋጠመው “ግሪዳው” ከስድስት ወራት በላይ ከሜዳ ርቆ የቆየ ሲሆን ለሦስት ወራት በግል ጂም እየሰራ መቆየቱንና በቀናት ውስጥ ወደ ሜዳ ልምምድ እንደሚመለስ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

“የጉዳት ጥሩ የለውም” የሚለው አብዱራህማን ከሜዳ መራቁ ተፅእኖ እንደፈጠረበት ገልጾ ወደ ሜዳ ሲመለስ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀው አልሸሸገም። ” ፋሲል ከነማ ያለበት ወቅታዊ አቋም በጣም ጥሩ እየሄደ ነው። እና እንደሚታየው ቀላል አይሆንም፤ ባለው ነገር እኔም ከጉዳት እንደመመለሴ ብዙ ስራ እንደሚጠብቀኝ አውቃለሁ። ግን ሁሉንም ተቋቁሜ የራሴን ነገር ክለቡ ላይ ማሳረፍ እፈልጋለሁ። የተሻለ ነገር ለመስራት ነው እያሰብኩ ያለሁት።” ብሏል።

ፋሲል የዋንጫ ባለቤት በሆነበት የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ላይ የትከሻ ጉዳት ያስተናገደው እንየው ካሣሁን በአሁኑ ወቅት በዮርዳኖስ ሆስፒታል ህክምናውን እየተከታተለ ይገኛል።

ፈጣኑ የመስመር ተከላካይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት በጥር ወር ወደ ሜዳ ሊመለስ እንደሚችል ገልጿል። ” አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለው። ከፍተኛ ለውጥም እየተመለከትኩ ነው። የፊታችን ታኀሳስ 25 ቀን የሀኪም ቀጠሮ አለኝ። በቀጣይ እነርሱ የሚሉኝንም እሰማለሁ፤ በእኔ እምነት ግን አሁን ካለኝ ጤና አንፃር ጥር ወር ላይ ወደ ሜዳ እመለሳለው ብዬ አስባለው።” ብሏል።

ሰለሞን ሀብቴ ሌላው ወደ ሜዳ ለመመለስ የተቃረበ ተጫዋች ነው። ክረምት ላይ የጉልበት መገጣጠሚያ ጉዳት ካስተናገደ ወዲህ ከሦስት ወራት በላይ ከሜዳ የራቀው ሰለሞን ሀብቴ በግሉ ልምምድ እየሰራ እንዳለ በመግለፅ በቅርቡ ከቡድኑ ጋር እንደሚቀላቀል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

ዐምና በተለያዩ ሚናዎች ላይ በርካታ ጨዋታ ያደረገው ሰለሞን ወደ ሜዳ ከተመለሰ በኋላም እንደ ዐምናው ሁሉ በተሰጠው ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። ” በመጀመሪያውም አመት ስመጣ ክለቡን ለማገልገል ነበር። ዐምና በርካታ ቦታዎች ላይ ተሰልፌ እጫወት ነበር። ዘንድሮም በጎደለው ቦታ ገብቼ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ። ምክንያቱም አላማዬ ክለብን ማገልገል ነው።” ብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ