በሳምንቱ ከሚጠበቁት ጨዋታዎች መካከል የአንድ ከተማ ክለቦቹ የደርቢ ጨዋታን በተከታዩ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
ሲዳማ ቡና ዐምና መቀመጫውን እና የሚጫወትበት ሜዳን ወደ ሀዋሳ ካዞረ በኋላ ወደ ሀዋሳ ከተማ ደርቢነት የተሸጋገረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፈጣን አንቅስቃሴ እና ደማቅ ድባብ የታጀበ ፍልሚያን እንደሚያስመለክተን ከወዲሁ ይጠበቃል።
ከጥሩ አጀማመር በኋላ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከባድ ሽንፈት የደረሰባቸው ሀዋሳዎች ማገገምን ቀዳሚ ትኩረት አድርገው ወደ ሜዳ የሚገቡ ሲሆን ወደ ጥሩ ጎዳና ለመመለስ ተጠባቂውን ጨዋታ ማሸነፍ ትልቅ መነሳሻ ይሆናቸዋል።
ለወትሮው ለመከላከል አደረጃጀት ቅድሚያ በመስጠት በመልሶ ማጥቃት ሲጫወት የሚስተዋለው ሀዋሳ ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ባልተጠበቀ መልኩ በጀብደኝነት በማጥቃት ለመጫወት ማሰባቸው ተጋላጭነቱን ጨምሮት ታይቷል። በኢትዮጵያ ቡና ፈጣን ሽግግሮችም በአግባቡ ተቀጥቷል።
ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ከተስተዋለበት ድክመቱ መነሻነት፤ እንዲሁም በዚህ ሳምንት የሚገጥመው ሲዳማ ቡና እንደመሆኑ ከተከላካይ ጀርባ ክፍተቶችን ካገኘ አይምሬ የሆነ የአጥቂ ጥምረትን ለማቆም እንደቀደሙት ጊዜያት ወደኃላ ሰብሰብ ብሎ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ተቀዳሚ ምርጫ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ሀዋሳ መሳይ ጳውሎስ እና መስፍን ታፈሰን ከጉዳት፣ ወንድማገኝ ማዕረግን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ እስራኤል እሸቱ እና ቸርነት አውሽን በጉዳት አይሰልፍም፡፡
እንደከተማ ተቀናቃኙ ሁሉ ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ያስተናገደው ሲዳማ ቡና የዐምናው ተፎካካሪነቱን ይዞ ለመዝለቅ ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥቦች ይዞ መውጣትን በማለም ወደ ሜዳ ይገባል።
ሀዋሳ ላይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በርካታ ጎሎች ለማስቆጠር የማይቸገረው ሲዳማ ቡና አሁንም ከወገብ በላይ ባሉት ተጫዋቾች ላይ እምነቱን ጥሎ ወደ ሜዳ ይገባል። እንደተጋጣሚው የጨዋታ አቀራረብ ቢወሰንም ቡድኑ በሁለቱም መስመሮች የሚያደርገው ፈጣን እና ሚዛናዊ የማጥቃት እንቅስቃሴ በነገው ጨዋታ በተመሳሳይ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ከሆነው ሀዋሳ ከተማ ፉክክር እንደሚገጥመው ሲጠበቅ በዳዊት ተፈራ አማካኝነት መሐል ለመሐል የሚደረጉ ጥቃቶች ተጨማሪ አማራጭ እንደሚሆን ይገመታል።
ሲዳማ ቡና ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ርቆ የቆየው አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩ እና አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስ ያገገሙለት ሲሆን ሚሊዮን ሰለሞን አሁንም በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 20 ጊዜ ተገናኝዋል። ሲዳማ ቡና 7 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዋሳ 5 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– ቡድኖቹ ሀዋሳ ስታዲየም ላይ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ስንመለከት 11 ጊዜ ተገናኝተው 6 የአቻ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ሲዳማ 3 ሲያሸንፍ ሀዋሳ 2 አሸንፈዋል።
– በአጠቃላይ 20 ግንኙነቶቻቸው 42 ጎሎች ሲቆጠሩ ሲዳማ 23፣ ሀዋሳ 19 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-4-2)
ቤሊንጋ ኢኖህ
ዳንኤል ደርቤ – ላውረስ ላርቴ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ያኦ ኦሊቨር
ብርሃኑ በቀለ – ተስፋዬ መላኩ – አለልኝ አዘነ – መስፍን ታፈሰ
ብሩክ በየነ – የተሻ ግዛው
ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)
መሳይ አያኖ
ዮናታን ፍሰሀ – ጊት ጋትኮች – ግርማ በቀለ – ግሩም አሰፋ
አበባየው ዮሀንስ – ብርሀኑ አሻሞ
አዲስ ግደይ – ዳዊት ተፈራ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
ይገዙ ቦጋለ
© ሶከር ኢትዮጵያ