ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ባህር ዳር ከተማ

በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ነገ አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ላይ የሚደረገውን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

አዲስ አዳጊው ሀዲያ ሆሳዕና እስካሁን በሊጉ ሙሉ ሦስት ነጥብ ካላገኙ ሁለት ክለቦች (ጅማ አባጅፋር ሌላው ነው) አንዱ ነው። በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ቡድኑ በነገው ጨዋታ የመጀመርያ ድሉን ለማግኘት አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

እንደ ድሬዳዋ ከተማ እና ስሑል ሽረ ሁሉ የተዳከመ የተከላካይ መስመር ያለው ቡድኑ በነገውም መርሐ ግብር በአራት ጨዋታ ሰባት ጎሎች ካስቆጠረው ባህር ዳር ከተማ ፈተና እንደሚጠብቀው ተገምቷል። በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ጎንደር አምርቶ ሦስት ጎሎች ከተቆጠረበት የፋሲሉ ጨዋታ የአጨዋወትም ሆነ የተጫዋች ለውጦችን የማያደርግ ከሆነ ጨዋታው ከባድ ሊሆንበት ይችላል።

በመሃል ሜዳ ላይ ከተጋጣሚው የተሻለ የቁጥር ብልጫ ለማግኘትና የተከላካይ መስመሩን ሽፋን ለመስጠት የአማካይ መስመር ተጨዋቾች በማብዛት ለጨዋታው እንደሚቀርብ የሚገመት ሲሆን እስካሁን ውጤታማነቱን ያላሳየውና በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ለውጦች እየታየበት የሚገኘው የአጥቂ መስመር ላይ አሁንም ብዙ ሥራዎች ይጠብቁታል።

ከደካማ ጎኖቹ ባሻገር በአየር ላይ ኳሶች ጥሩ የሆኑ ተጨዋቾችን በመያዙ አጨዋወቱን በረጃጅም ኳሶች በመቃኘት ለተጋጣሚ ፈታኝ ለመሆን እንደሚጥር ይታሰባል። በተጨማሪም በተሻጋሪ ኳሶች ላይ አደገኛ የሆነው ባህር ዳር ከተማን ለመቆጣጠር የአየር ላይ ኳሶች አንፃራዊ ጥንካሬው አጋዥ ሊሆንለት ይችላል።

የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች አብዱልሰመድ ዓሊ በጉዳት የመስመር ተጫዋቹ ሱራፌል ዳንኤል ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

የፋሲል ተካልኝ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው ያገኘውን የ4-1 ድል ለማስቀጠል ለጨዋታው ይቀርባል። ካደረጋቸው ሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች (አዳማ ላይ ጅማን እንዲሁም ሃዋሳ ላይ ሃዋሳን የገጠመበት) አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካት የቻለው ቡድኑ ይህንን ከሜዳ ውጪ ያለውን አይናፋርነት ለመስበር ወደ ሜዳ ይገባል። በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የተሟላ የሚመስለው ቡድኑ በነገው ጨዋታ በሚታወቅበት የኳስ ቁጥጥር እንደሚዘልቅ ይገመታል።

በነገው ጨዋታ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ 11 ሁለት ጊዜ መግባት የቻለው ፍፁም ዓለሙ ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ እንደሚሆን ይታሰባል። ኳስ የሚያደራጅበት እና ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚሮጥበት መንገድ እንዲሁም ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን ለቡድን አጋሮቹ የሚፈጥርበት ሂደት በነገው ጨዋታ ለሃዲያዎች ፈተና ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ከዚህ ውጪ ፈጣኖቹ ወሰኑ ዓሊ እና ግርማ ዲሳሳ የሚያደርጉት ፈጣን የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ለቡድኑ ጥንካሬን ይሰጡታል።

ተጋባዦቹ የተሟላ ስብስብ ቢኖራቸውም በየጨዋታው ግብ የሚያስተናግዱበት ጉዳይ በነገው ጨዋታ ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ያሰጋል። ከአራቱ የሊጉ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግብ ሳያስተናግዱ (የጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ) የወጡት ባህር ዳሮች ምናልባት በነገው ጨዋታም ከተጋጣሚያቸው ጫናዎች ከበዙባቸው ግብ ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥቷል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ከዚህ በፊት ፕሪምየር ሊጉ እርስ በእርስ ተገናኝተው የማያውቁት ሁለቱ ቡድኖች ነገ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-2-3-1)

አቤር ኦቮኖ

ፍራኦል መንግስቱ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቃታ – ሄኖክ አርፊጮ

አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንደሻው

ቢስማርክ አፒያ – በኃይሉ ተሻገር – ኢዮኤል ሳሙኤል

ቢስማርክ ኦፖንግ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሄሱ

ሳላምላክ ተገኝ – አዳማ ሲሶኮ – አቤል ውዱ – ሚኪያስ ግርማ

ፍፁም ዓለሙ – ፍ/ሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን

ግርማ ዲሳሳ – ማማዱ ሲዲቤ – ወሰኑ ዓሊ


© ሶከር ኢትዮጵያ