በነገው ዕለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ስሑል ሽረ በሜዳው አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበትን መርሐ ግብር እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በቡድኑ ከወገብ በላይ ተሰላፊ የሆኑ ወሳኝ የውጭ ዜጋ ተጫዋቾቹን ሳይዙ ከሜዳቸው ውጪ ወሳኝ አንድ ነጥብ ይዘው የተመለሱት ሽረዎች በጨዋታ በአንድ ወጥ መስመር የሚጫወት የኋላ ተከላካይ መስመር እንዲሁም ከፊታቸው ደግሞ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ለመውጣት ፍላጎት በሌላቸው አማካይ ተጫዋቾች የተዋቀረው የመሀል ሜዳ ጥምረት ለተጋጣሚ እጅግ ፈታኝ ሆኖ ተስተውሏል።
ቡድኑ በዚህኛው ሳምንት ግን ጨዋታውን በሜዳቸው የሚያደርጉ ከመሆኑ አንፃር በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከተከተሉት ፍፁም መከላከል የተለየ አቀራረብ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በተለይ በደሞዝ ምክንያት ያልተሰለፉት ተጫዋቾችን መልሰው ማግኘታቸው በንፅፅር የተሻሉ በሆኑበት የመስመር ማጥቃት ላይ ትኩረት ኤንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የባለፈው ሳምንት የአማካይ ጥምረትን ጨምሮ አመዛኞቹን ተጫዋቾች በድጋሚ ይጠቀማሉ ተብለው የሚጠበቁት ሽረዎች ከፈረሰኞቹ ጋር በነበረው ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣው ዮናስ ግርማይን በቅጣት ሲያጡ ዲዲዬ ለብሪ እና ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ምንተስኖት አሎን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ይመልሳሉ ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በደሞዝ ምክንያት ያጣቸው አራት ተጫዋቾች መልሶ ሲያገኝ በጉዳት የሚያጣው ተጨማሪ ተጫዋች የለም።
ባለፈው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ በተለያዩበት የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ግብ ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች በዚህ ዓመት በሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው አንድ ጨዋታ በማሸነፍ ስድስት ነጥቦች ሰብስበዋል። ባለፉት ጨዋታዎች የሦስት እና የአራት የተከላካዮች ጥምረትን አፈራርቀው ሲጠቀሙ የነበሩት አዳማዎች በነገው ጨዋታ በሦስት ተከላካይ ወደ ጨዋታው ይገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ እንደተለመደው በፈጣን አጥቂዎቻቸው ላይ መሰረት ያደረገ የማጥቅያ መንገድ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ቡድኑ ፊት መስመሩ ላይ የአጥቂዎቹን ፍጥነት በመጠቀም ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር እንደሚጥር ሲጠበቅ በዚህ ረገድ የሚታይ ድክመት ያለበት ሽረን የተከላካይ መስመር እንደሚፈትኑ ይገመታል።
አዳማዎች ሚካኤል ጆርጅን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ዐመለ ሚልክያስ እና አማኑኤል ጎበና በጉዳት ምክንያት ወደ መቐለ ያልሄዱ ተጫዋቾች ናቸው።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች ሁለት ጊዜ (ዐምና) በሊጉ ተገናኝተው ሽረ ላይ ያለ ጎል ሲለያዩ አዳማ ላይ አዳማ 4-1 ማሸነፉ ይታወሳል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ምንተስኖት አሎ
ዓብዱሰላም አማን – በረከት ተሰማ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሽዋለም – ነፃነት ገብረመድህን – ሙሉዓለም ረጋሳ
ዲዲዬ ለብሪ – ብሩክ ሐድሽ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ
አዳማ ከተማ (3-4-3)
ጃኮ ፔንዜ
መናፍ ዐወል – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ
ፉአድ ፈረጃ – አዲስ ህንፃ – ከነዓን ማርክነህ – ሱሌይማን ሰሚድ
በረከት ደስታ – ቡልቻ ሹራ – ዳዋ ሆቴሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ