ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ተለያይቷል

በአምሰተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዲያ ሆሳዕና ባህር ዳር ከተማን አስተናግዶ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በፋሲል ከነማ ከተሸነፉበት ስብስብ በቅጣት ሱራፌል ዳንኤልን እንዲሁም በጉዳት አብዱሰመድ ዓሊን በማስወጣት በምትኩ በረከት ወልደ ዮሐንስ እና ዮሴፍ ደንገቱን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ አካተዋል። በአንፃሩ ባህር ዳር ከተማዎች በሜዳቸው ድሬዳዋ ከተማን ከረቱበት ስብስስ ውስጥ ሳሙኤል ተስፋዬ፣ አቤል ውዱ እና ሳምሶን ጥላሁንን አስወጥተው በምትካቸው ሰለሞን ወዴሳ፣ ዳንኤል ኃይሉ እና ሳለአምላክ ተገኝን አሰልፈዋል።

ላለፉት አምስት ሳምንታት እረፍት ባላገኘው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም የተካሄደው የነብሮቹ እና የጣና ሞገዱቹ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የሆሳዕና ደጋፊዎች ማኅበር ለባህዳር ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የሆሳዕናን ባህላዊ የአንገት ልብስ በስጦታ አበርክተዋል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጀምሮ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የጀመሩት ባለሜዳዎቹ በ1ኛው ደቂቃ ቢስማርክ አፒያ ባደረገው ሙከራ የባህር ዳር ከተማዎችን ግብ ፈትሸዋል። ነብሮቹ በ2ኛው ደቂቃ እዮብ በቀታ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ወደግብ አክሮሮ መትቶ በግቡ አናት በወጣችበት እንዲሁም በ14ኛው ደቂቃ ከበረከት ወልደዮሐንስ የተሻማውን ቢስማርክ አፒያ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ከሁለት ተከላካዮች መሀል ውስጥ ሆኖ በመምታት ወደላይ በሰደደው ሙከራዎች ቀዳሚ ለመሆን የቀረቡ እድሎችን ፈጥረዋል።

ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል ወደ ሆሳዕና ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ባህር ዳሮች በሰባተኛው ደቂቃ ግርማ ዲሳሳ ያሻማውን ኳስ ሲዲቤ በመግጨት የመጀመሪያውን ሙከራ ሲያደርጉ ከተደጋጋሚ ያልተሳኩ ረጃጅም ኳሶች በኋላ በ30ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ የተሻገረውን ማማዱ ሲዲቢ ወደ ግብነት በመለወጥ እንግዶቹን በግብ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት የነበረው የጣናዎቹ ሞገዶች እንቅስቃሴ ሌላ የግብ እድሎችን ሳያስመለክተን የመጀመሪያው አጋማሽ ሲገባደድ በአንፃራዊነት ሆሳዕናዎች የተሻሉ የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት አዩብ በቀታ ከርቀት የመታው እና የግቡን አግዳሚ ለትሞ የተመለሰው ኳስም እጅጉን ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ረዣዥም ኳሶች በዝተውበት እና ማራኪ እንቅስቃሴ ሳይታይበት የዘለቀ ቢሆንም ሦስት ጎሎች የተቆጠሩበት አጋማሽ ነበር።

ባለሜዳዎቹ ገና ከጅምሩ የአቻነት ግብ ፍለጋ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በቶሎ ጎል ማግኘትም ችለዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ቢስማርክ ኦፖንግ በግንባሩ በመግጨት ባለሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ሆኖም አቻነቱ የዘለቀው ለ3 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 52ኛው ደቂቃ ላይ የማዕዘን ምት ለመሻማት ነቅለው የወጡትን የሆሳዕና ተጫዋቾች ክፍተት በመጠቀም በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ማማዱ ሲዲቢ በአግባቡ በመግፋት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሲመታው ኦቮኖ ቢመልሰውም ፍፁም ዓለሙ በመምታት ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የስታዲየሙ ድባብ ወደ ፀጥታ የተለወጠ ሲሆን የጨዋታውም እንቅስቃሴ እጅጉን ተቀዛቅዟል። ባህር ዳሮች ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ትኩረታቸውን በራሳቸው ሜዳ ብቻ በማድረግ ሲንቀሳቀሱ በተቃራኒው ሆሳዕናዎች ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች በድጋሚ የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። በዚህም በ70ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ የተሻማውን ቅጣት ምት ደስታ ጊቻሞ በግንባሩ በመግጨት የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።

በአቻነት ጎሉ ይበልጥ የተነቃቁት ሆሳዕናዎች ተቀይሮ በገባው ፍራኦል ተሻጋሪ ኳሶች እና ከርቀት በሚሞከሩ ሙከራዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። አፈወርቅ ኃይሉ እና ይሁን እንደሻው ከርቀት መትተው ግብጠባቂው ሀሪስን ያወጣባቸው ኳሶችም የሚጠቀሱ ነበሩ። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎሎች ሳይቆጠሩ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው የሆሳዕናው ግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና የባህር ዳር አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የቃላት ልውውጥ ሲያደርጉ የታየ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ ጥቂት ደጋፊዎች ሜዳ ውስጥ በመግባት ዳኛው ላይ ተቃውሞ ቢያሰሙም የሆሳዕና ደጋፊ ማኅበር አባላት በቶሎ መቆጣጠር ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ