በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዲያ ሆሳዕና ከ ባህር ዳር ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ቡድን ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
” ከተከታታይ ሽንፈት በኃላ ነው ያደረግነው ጨዋታ እንደመሆኑ ጫና ውስጥ ሆነን ነው የተጫወትነው” – ግርማ ታደሰ (ሀዲያ ሆሳዕና)
” ከተከታታይ ሽንፈት በኃላ ነው ያደረግነው ጨዋታ እንደመሆኑ ትንሽ ጫና ውስጥ ሆነን ነው ጨዋታውን ያደረግነው። ከዚህ ለመውጣት በቂ ዝግጅት አድርገን ነበር። የመጀመሪያውን አጋማሽ እንደፈለኩት መጫወት አልቻልንም ነበር፤
ተጫዋቾቼ ጫና ውስጥ የነበሩ በመሆናቸውም ጨዋታችን ተበላሽቶብን ነበር። በጨዋታው የገቡብን ጎሎች የትኩረት ማነስ ችግሮች ናቸው። ተጫዋቾቼ ችሎታ አላቸው፤ ነገር ግን ትኩረት በማጣታችን ሁለቱም ጎል ገብቶብናል።
” ተጋጣሚያችን በመልሶ ማጥቃት ነበር የሚጫወተው። አብዛኛውን ደቂቃ ብንይዛቸውም ራሳችን በሰራናቸው ስህተቶች ግቦች ተቆጥርበውናል። በሁለተኛው አጋማሽ በእጅጉ ተሻሽለን በመግባት በእንቅስቃሴ የተሻልን ነበርን። በአጠቀላይ ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነበር። በእኛ በኩል ውጤቱን ለመቀልበስ እንዲሁም ተጋጣሚያችን መሪነቱን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ያሳከበት ነው። በቀጣይ ወደ ሙሉ አሸናፊነት እንመለሳለን።”
“ረጅም ርቀት ተጉዘው የደገፉን ደጋፊዎቻችን ማመስገን እፈልጋለሁ” – ፋሲል ተካልኝ (ባህርዳር ከተማ)
” ጨዋታው ረጃጅም ኳስ እና ጉልበት የበዛበት ጨዋታ ነበር። ሁለተኛውን ግብ ካስቆጠርን ባኃላ ተጋጣሚያችን ተጭነው ተጫውተዋል። ቡድናችን በመጀመሪያው አጋማሽ ተጨማሪ ግቦችን በማግባት ጨዋታውን መግደል እንችል ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቷል። ተጫዋቾቼ ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት የአቅማቸውን ጥረዋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል።
” ስለ ሜዳው ምንም ማለት ባልፈልግም ለዚህ ሜዳ የሚሆን አጫዋወት ይዤ መጥቻለሁ። ይሄን ተግብረን ወጥተናል። ከሜዳ ውጭ እንደመሆኑ አንድ ነጥብ ማግኘት አይከፋም። በስተመጨረሻም ደጋፊውን አመስግናለው፤ ጥሩ ደጋፊ ነበር። ረጅም ርቀት ተጉዘው ለደገፉን ደጋፊዎቻችን ማመስገን እፈልጋለሁ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ