በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት መቐለ ላይ በስሑል ሽረ እና አዳማ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። የዱላ ሙላቱ የመጨረሻ ሰዓት ግብም አዳማ ከተማን ከመሸነፍ ታድጋለች።
ባለሜዳዎቹ ከባለፈው ሳምንት አሰላለፋቸው ወንድወሰን አሸናፊ፣ መድሃኔ ብርኃኔ እና ዮናስ ግርማይን (ቀይ) በምንተስኖት አሎ፣ በረከት ተሰማ እና ዲድየ ሌብሪ ተክተው ሲገቡ አዳማ ከተማዎች ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ጃኮ ፔንዜ፣ ፉአድ ፈረጃ፣ ቡልቻ ሹራ እና ዱላ ሙላቱን በደረጄ ዓለሙ፣ ሱሌይማን ሰሚድ፣ ሱሌይማን መሐመድ እና ብሩክ ቃልቦሬ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው አንፃር የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉት ባለሜዳዎቹ ሽረዎች በተለይም ጫና በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ዲድየ ለብሪ መቶት ቴዎድሮስ በቀለ ተደርቦ ያወጣው እና ዓብዱለጢፍ መሐመድ ከመስመር አሻግሮት ደረጄ ዓለሙ እንደምንም ያዳነው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
ረመዳን ናስር እና ዓብዱለጢፍ መሐመድ በተሰለፉበት መስመር በኩል የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሽረዎች በተጠቀሰው ቦታ ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በተጫዋቾች ያልተሳካ የመጨረሻ ኳስ ውሳኔ ምክንያት ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በዚህም ዓብዱለጢፍ መሐመድ ብሩክ ሐድሽ ከመስመር ያሻማው ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና ሀብታሙ ሽዋለም ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶ ወደ ውጭ ከወጣው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።
በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከኳስ ቁጥጥር አልፈው ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩት አዳማዎች ዘግይተው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ በመግባት ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም የቡድኑ የክንፍ ተጫዋች (Wing back) ሱሌይማን ሰሚድ በማጥቃቱ ላይ የነበረው ተሳትፎ የሚበረታታ ነው። ቡድኑ ካደረጋቸው ሙከራዎችም በረከት ደስታ ሱሌይማን ሰሚድ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ጥሩ ሙከራ እና ከነአን ማርክነህ ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት ሞክሮት ተከላካዮች የመለሱት ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
ከመጀመርያው አጋማሽ በቁጥር ያነሱ ሙከራዎች የታዩበት እና በበርካታ የተጫዋቾች ሹክቻ ታጅቦ የተካሄደው ሁለተኛው አጋማሽ ጎሎች ቢቆጠሩበትም ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር። በአጋማሹ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ስሑል ሽረዎች ሲሆኑ ዲድዬ ሌብሪ በመልሶ ማጥቃት ሄዶ ለብሩክ ሐድሽ አሻግሮለት አጥቂው መቶ ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውታል። ብዙ ሳይቆዩም በ50ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ሽዋለም የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምትን በአግባቡ በመጠቀም አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ በኋላ ወደ ፈጣን አጥቂዎቻቸው በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት አዳማዎች በሁለት አጋጣሚዎች በቡልቻ ሹራ እና በረከት ደስታ አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተለይም ቡልቻ ሹራ በተከላካዮች የትኩረት ማጣት ያገኘውን ኳስ ተጠቅሞ ያመከናት ወርቃማ ዕድል አስቆጪ ነበረች። ጨዋታው ቀጥሎ በዚህ ውጤት ይገባደዳል ተብሎ ሲጠበቅ በ88ኛው ደቂቃ ዱላ ሙላቱ የግብ ጠባቂው ምንተስኖትን መውጣት ተመልክቶ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ውጤትን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ለተከታታይ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ