የአሰልጣኞች አስተያየት| ሀዋሳ ከተማ 1-3 ሲዳማ ቡና

በአምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለቱን የሀዋሳ ክለቦች ያገናኘው የሀዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ በሲዳማ ቡና 3ለ1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኃላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ተከታዩን ብለዋል፡፡
“የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገን ነው ያሸነፍነው” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለጨዋታው

አንደኛ ሁለታችንም ከሽንፈት መልስ ነው የተገናኘነው። ከዛ ውጪ ደርቢ ነው። የአንድ ከተማ ክለቦችም ነን፤ ስለምንተዋወቅም በታክቲክ ደረጃ ማርኪንግ የበዛበት ጨዋታም ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ እኛ ውጤታማ ነበርን። ያገኘነውን አጋጣሚዎች ተጠቅመናል፤ ይዘነው የገባነውን ታክቲክ በየቦታው ተግባራዊ አድርገናል። አማካዩም ላይ፣ አጥቂም ላይ፣ ተከላካዩም ላይ በተደጋጋሚ ይሰራብን የነበረው ስህተት አርመን ገብተናል። እና የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገን ነው ያሸነፍነው ማለት ይቻላል፡፡

መሀል ሜዳ ላይ የዳዊት ተፈራ መቀዛቀዝ

የዳዊት ጠንካራ ጎን ስለሚታወቅ ኳሱን በሚይዝበት ሰዓት የነሱ የተከላካይ አማካይ ይይዘው ነበር። የመጫወት ዕድሉንም በዚህ የተነሳ አላገኘም። በተቃራኒው ግን እሱም ተመሳሳይ ነገርን ነበር ሲያደርግ የነበረው። ሁለቱም እዛ ጋር የመታየት ዕድል አላገኙም። ዞሮ ዞሮ ዳዊት ወደ ኃላ ዞሮ በሚጫወትበት ሰአት የነሱ የተከላካይ አማካይ በነፃነት ይጫወት ነበር፡፡ የተደረገው ታክቲክ ነው፡፡

ስለ ረጃጅም እና የሚባክኑ ኳሶች

“ይሄ ከእረፍት በፊት የተፈጠረ ነው። መበላሸቱ ይህ ደግሞ የተፈጠረው ከሽንፈት መልስ ስለመጣን ቶሎ አሸንፈን ከመመለስ አንፃር የመጣ ነውና ከእረፍት በኃላ ግን አስተካክለናል፡፡ የሚባክኑም አልነበሩም።


“በኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ላይ የሰራነውን ስህተት ነው ዛሬም የሰራነው” አዲሴ ካሳ (ሀዋሳ ከተማ)

ስለጨዋታው

” ልክ ኢትዮጵያ ቡና ላይ የሰራነውን ስህተት ነው ዛሬም የሰራነው። ከኃላ መስመራችን ከበረኛው ጀምሮ ስህተት ነበር፤ ቡና ላይም ሁለተኛው ግብ ሲቆጠር ይኸው ስህተታችን ነበር። የታየው የዛሬው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ግቦች ታይሚንግ የመጠበቅ ስህተት ነው። ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዋል፤ ይህ የእግር ኳስ ህግ ነው፡፡ ስለ ልቦናው ላይ መስራት አለብን፤ የተጫዋቾች ጭንቅላት ላይም መስራት አለብን። የሆነ ክፍተት ተጫዋቹ ጋር ይታየኛል፡፡ ለመጫወት አዕምሮህ ፍቃደኛ ካልሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከቡና ጋር ያየውትም ሆነ ዛሬም ያየውት ተመሳሳይ ነው፡፡ የኛ ተከላካይ እንዲህ ታልፎ የሚገባበት አልነበረም፡፡ አሁን ግን ሁለቱም ጨዋታ ላይ ያየነው ይሄ ነው፡፡ ከተጫዋቹ ጋር በዚህ ላይ ማውራት አለብን መልስም ይፈልጋል፡፡

የማጥቃት ፍላጎት ማጣት እና ተጫዋች ምርጫ

ውጤት ያለመፈለግ አይደለም፤ ዳንኤልን የባህር ዳር ጨዋታ ላይ አይተናል። ከዛም በፊት በነበሩት ላይ ተመልክተነዋል። የዳንኤልን ኳስን እኛ መጠቀም አልቻልንም። አሁንም ከመስመር የሚነሱ ኳሶች ብዙ ናቸው፡፡ ግን ተጠቃሚ ተጫዋች እዛ ጋር ከሌለ የዳንኤል መኖር ምንም ጥቅም የለውም። በዛ ቦታ ያስገባነው አክሊሉን ነው፡፡ አክሊሉ የተሻለ ወደ ግብ ሰብሮ የመግባት አቅም አለው፤ የታየውም ነገር እሱ ነው፡፡ ከዛ አንፃር ነው።

ሁለታችንም የአንድ ከተማ ቡድኖች ስለሆንን በደንብ እንተዋወቃለን፡፡ ስለዚህ ዳንኤልን መጀመሪያ ብናሰልፈው ከዳንኤል የሚነሱትን ኳሶች በደንብ ስለሚያውቁት ይቆጣጠሩታል የሚል ግምት ነበረን እና ከዛ አንፃር ነው፡፡ እንጂ ውጤት አለመፈለግማ እንዴት ይሆናል፡፡ እነሱ በቃ ያገኙትን አጋጣሚ ነው የተጠቀሙት። በተለይ ከእረፍት በኃላ ሁለት የተጣለ ኳስ ገባ። እዛ ጋር ማስተካከል አለብን የኃላ መስመራችን የኛ እንዲህ አደለም የመጠባበቅ ነገር ነበር ላውረንስ አጠባበቁ ጥሩ ነው፡፡ አሁን ግን ሁለቱም ጨዋታ ላይ ይሄንን አላየውባቸውም። የኋላ መስመራችን ላይ ክፍተት ይታየኛል፡፡ ምናልባት መሳይ በቀጣይ ይኖራል፤ የሱ መኖር እነኚህን ነገሮችን በተወሰነ ይቀርፍልናል ብዬ አምናለሁ። አዲስዓለምን ያስቀመጥነው ካለፈው ጨዋታ ብቃቱ አንፃር ነው፡፡ በአጠቃላይ እንድንሸነፍ የሆነው እንደ ቡድን ሳይሆን በግል ስህተቶች ነው፡፡

አክሊሉን (የተሻለ ስለሆነ ነው የተጠቀምነው ብለሀል) ግን ሲጠቅም አላየንም…

ትክክል ነው፤ አክሊሉ ከሦስት እና አራት ጨዋታ በኋላ የገባ ነው። አክሊሉን ካየነው ኳስ የማስጣል አቅሙ ድሪብሉ የመሄድ ወደፊት አቅሙም ሙሉ ነበር፡፡ ከሶስት እና አራት ጨዋታ በኃላ ስለገባ ግን ክፍተት አይተንበታል፡፡ ወደ መጨረሻዎቹ ድክም ያለ ነገር ታይቶበታል፡፡ ይሞክራል፤ ይዘጋበታል። የተዘጋ ቦታ ላይ ነው ለማለፍ የሚሞክረው። የኛ ተጫዋቾች ላይ በአጠቃላይ ያየንባቸው ይሄ ነው። መሄድ እንፈልጋለን፤ ይዘጉብናል፡፡ እነሱ በደንብ የተዋጣላቸው ናቸው፤ ተዘጋጅተውበታል። ያን ማስተካከል አለብን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ