ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድሉን ወላይታ ድቻ ላይ አሳክቷል

በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሶዶ ላይ ወልቂጤ ከነማን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 1-0 ተሸንፏል። አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማም በታሪኩ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ የሜዳ ውጪ ድል ማስመዝገብ ችሏል።

ወላይታ ድቻ ባለፈው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ቸርነት ጉግሳ እና ተስፋዬ አለባቸውን በተመስገን ታምራት እና ፀጋዬ ብርሃኑ ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ፤ እንግዳው ወልቂጤ ከተማ በሰበታ ሽንፈት ካስተናገደበት አሰላለፍ ውስጥ የስድስት ተጫዋችን ለውጥ በማድረግ ይድነቃቸው ኪዳኔ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ፣ ይበልጣል ሽባባው፣ አ/ከሪም ወርቁ፣ ሄኖክ አወቀ እና አቤኔዘር ኦቴ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተው ሶሆሆ ሜነሳህ፣ መሐመድ ሺፋ፣ አዳነ በላይነህ፣ ፍፁም ተፈሪ፣ ዓባይነህ ፌኖ እና አህመድ ሁሴንን ወደ ተጠባባቂ እና በጉዳት ከአሰላላፍ ውጪ ያደረጓቸው ተጫዋቾች ናቸው።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ብዙም ማራኪ ያልነበረ እና አልፎ አልፎ ድቻዎች ኳሱን ለመቆጣጠር ከሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም ወልቂጤዎች በመልሶ ማጥቃት በሁለቱም መስመሮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙም የተደራጀ አልነበረም።

በሙከራ ደረጃ ግን በ9ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ በቀኝ መስመር ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ ወደ ግብ ሞክሮ ይድነቃቸው ኪዳኔ ሲያድንበት በ13ኛው ደቂቃ ላይ እንግዶቹ ወልቂጤ ከተማዎች በአቤነዘር አቴ ድቻ ግብ ክልል ውስጥ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ወደ ጎል ቢሞክሩም መኳንንንት እንደምንም አድኗታል።

ከነዚህ ደቂቃዎች በኋላ ጨዋታው ቅርጽ ይዞ መካሄዱን የቀጠለ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ድቻዎች የወልቂጤን የተደራጀ የኋላ መስመር በቀላሉ ለመስበር ቢቸገሩም ከተስፋዬ አለባቸው በሚነሱ ኳሶች ወደ ግብ ለመቅረብ ሲሞክሩ ታይተዋል። በአንጻሩ ወልቂጤዎች ጥሩ የሆነ በማሐል ክፍል መናብብ መልሶ ማጥቃት በተለይም በግራ መሰመር በኩል ተሰልፎ ሲጫወት በነበረው ጫላ ተሺታ በተደጋጋሚ ወደ ድቻ የግብ ክልል በመግባት አደጋዎች ፈጥሯል። በተለይም በ31ኛው ደቂቃ ሰብሮ ገብቶ በመሞከር ወደ ውጪ ሲወጣበት በ34ኛው እና 35ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሰብሮ ገብቶ ለጃኮ አራፋት አመቻችቶ የሰጣቸው ኳሶች ጃኮ ቢሞክራቸውም በሚያሰቆጭ ሁኔታ መኳንንት አድኖበታል።

ጨዋታው በዚህ ሒደት ቀጥሎ የመጀርያውን እና ማሸነፊያውን ጎል በ41ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሄኖክ አወቀ ከመሃል ሜዳ የሰነጠቀለትን ኳስ ሌላኛው በዕለቱ ጥሩ የነበረው ጫላ ተሺታ የግሉን ጥረት በመጠቀም ከድቻ ሁለት ተከላካዮች በፍጥነት በማምለጥ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

የወልቂጤን የተደራጀ አጨዋወት ለመስበር ያለመ ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት ያደረጉት ድቻዎች ግልፅ የጎል እድል መፍጠር የተሳናቸው ሲሆን እዮብ ዓለማየው ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ለጥቂት ከግቡ አናት ላይ የወጣችበት የምትጠቀስ ሙከራ ነች።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ጥሩ ፉክክር የታየበት ሲሆን ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ግብ ለማስቆጠር ቀይረው ባስገቧቸው ዳንኤል ዳዊት እና ታምራት ስላስ ጫና ፈጥረዋል። እንግዶቹ ደግሞ ድንቅ በሆነ የመከላከል እና መሐል ሜዳው ላይ ተጠቅጥቀው ክፍተቶችን በመዝጋት ውጤት ለማስጠበቅ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል።

በድቻዎች በኩል 64ኛው ደቂቃ ላይ በቸርነት ጉግሳ የተሞከረውን ኳስ ይድነቃቸው ኪዳኔ በድንቅ ሁኔታ ሲመልሰው፣ በ75ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ያገኛትን እድል ሞክሮ በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። በ85ኛው ደቂቃ ላይ ታምራት ስላስ በቀኝ መስመር የላካት ኳስ ቸርነት ድንገት ቢያገኛትም ወደላይ የወጣችበት ሙከራም ለባለሜዳዎቹ አስቆጪ ሙከራ ነበረች።

በዚህ አጋማሽ ወልቂጤዎች ሊጠቀስ የሚችል የጎል እድል ባይፈጥሩም መሪነታቸውን ለማስጠበቅ በአራቱተከላካይ ተሰላፊዎቻቸው ጥምረት ድንቅ የሆነ የመከላከል ስራ ሲሰሩ ተስተውለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ የሜዳ ውጪ ድሉን ማስመዝገብ የቻለው ወልቂጤ ከተማ በ7 ነጥቦች ደረጃውን ወደ 7ኛ ከፍ ሲያደርግ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ወላይታ ድቻ ወደ 12ኛ አሽቆልቁሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ