የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-1 ወልቂጤ ከተማ

ወደ ሶዶ ያመራው ወልቂጤ ከተማ ባለሜዳው ወላይታ ድቻን ገጥሞ 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ለዛሬው ውጤታችን ሜዳው ትልቁን አስተዋጾ አድርጎልናል” ደግአረገ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታው እንዳያችሁት ከባድ ፉክክር ነበረው። እኛ ወደዚህ ስንመጣ የተቻለንን ነገር ተጠቅመን ውጤት ለማግኘት ነበር። ነገር ግን ወላይታ ድቻ ሊጉ ላይ ካሉት ጠንካራ ቡድኖች መካከል ነው፤ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችንም የያዘ ነው። ለዛም ነው ድቻ ከኛ በተሻለ ጥሩ የተጫወተው። ነገር ግን ለማሸነፍ ከነበረን አንፃር ጉጉት ማሸነፍ ይገባን ነበር። ሌላው ተጋጣሚያችንን እናከብራለን እንጂ ፈርተን አንመጣም። ለወላይታ ድቻም የተለየ ዝግጅት አላደረግንም።

ስለ ቀጣይ ጉዞ

እኛ እንደሚታወቀው ለሊጉ አዲስ ነን። ሊጉ እጅግ ፈታኝ፣ የገጠምናቸው ቡድኖችም ጠንካራ ናቸው። እዚህም የገጠመን ይሄ ነው። አሁን ግን ልጆቼ አሁን እየለመዱት ነው። አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ለዛሬው ውጤታችን ሜዳው ትልቁን አስተዋጾ አድርጎልናል። ከዚህ በፊት ሜዳው ሲተች እሰማ ነበር፤ እና በዚህ አጭር ጊዜ ሜዳውን አሻሽለው ማቅረባቸው በእውነት ሊመሠገኑ ይገባል።

“እኛ መቆጣጠር ያልቻልነው የመልሶ ማጥቃቱን ነው” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ወላይታ ድቻ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ለኛ ከጠበቅነው በታች ነበር የተጫወትነው። በመጀመርያ 15 ደቂቃ ጥሩ ነበርን፤ ነገር ግን ከዛ በኋላ ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ሳምንቱን ሙሉ በጣም ሰለፈለግን ተጫዋቾቼ ራሳቸውን ባለማረጋጋገታቸው የተነሳ እንደምናየው በኛ ስህህተት ጎል ተቆጥሮብናል። ይሄ ግን እኛን አያሳስበንም። ምክንያቱም ስህተት ያስተምረናል፤ ይሄም መማርያ ነው የሚሆነን። እኛ መቆጣጠር ያልቻልነው የመልሶ ማጥቃቱን ነው። በዛ ነው ተሸንፈን የወጣነው። ጎል ለማስቆጠር በብዛት ለማጥቃት ተጫዋቾቼ ይወጡ ነበር።

ስለ ሊጉ

እኔ ሊጉ ላይ ምንም ለውጥ አላየሁም። የኢትዮጽያ ሊግ አንድ ኩሬ ውስጥ ነው። እኔ ከፍተኛ ሊግ ነበርኩኝ እና ያው ናቸው። ምንም ልዪነት የላቸውም። የዘንድሮ ሊግ በመሠረታዊነት ሁለት ነገሮች ተሻሽለዋል። አንደኛው ነገር ሊጉ ላይ ሥርዓት እያየው ነው። የተኛውም ሜዳ ላይ ሁሉም ቡድኖች ወጤትን በፀጋ ተቀብሎ ነው የሚወጣው። ሁለተኛው ነገር አብዛኛው ቡድኖች ኳስ ለመጫወት ይሞክራሉ፤ ይሄ የሚያስደስት ነገር ነው።

በቀጣይ..

እኛ የያዝነውን ነገር ሳንለቅ እያሻሻልን ነው የምንደው። በአጭር ግዜ እያሻሻልን እንሄዳለን። እርግጠኛ ሆኜ የምነግራቹ ከዚህ በኃላ ሙሉ ቡድኔን አገኛለው፤ እና በደንብ እንቀየራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ