በአንጋፋው የድሬደዋ ስታድየም የተስተናገደው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን አገናኝቶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ድሬዎች ከአራተኛው ሳምንት የባህር ዳር ከተማ 4-1 ሽንፈት ማግስት ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን፣ ያሬድ ዘውድነህ እና ዘሪሁን አሼቦን በማሳረፍ ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ግብጠባቂው ሳምሶን አሰፋ፣ ፍሬዘር ካሳ እና ያሲን ጀማልን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአዲስ አበባ ስታድየም ከጨዋታ ብልጫ ጋር ሀዋሳ ከተማን 4-1 ከረቱበት ስብስባቸው ምንም ዓይነት የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የሁለቱ ቡድኖች አብሮነት እና መልካም ትስስር እንዲቀጥል በማሰብ ተጫዋቾች በባነር የተሰራ መልክቶችን በመያዝ ወደ ሜዳ ሲገቡ ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳው ውጭ የሚጫወት በማይመስል ሁኔታ 500 ኪሎ ሜትሩን አቋርጠው የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ለጨዋታው ድምቀት ሰጥተውታል።
ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ በመራው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥ ብልጫ የወሰዱበት፣ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የጎል ሙከራ የተመለከትንበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል። በክፍት እንቅስቃሴ አጋጣሚ በመፍጠር ጎል ለማስቆጠር የተቸገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ11ኛው ደቂቃ በፍቅረየሱስ አማካኝነት ከሳጥን ውጭ አጠንክሮ በመታው እና የድሬው ግብጠባቂ ሳምሶን አሰፋ በቀላሉ በያዛት ሙከራዎች የድሬን የኋላ መስመር ፈትሸዋል።
በተለመደው ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ፊት እና ወደ ኃላ በመመላለስ በሚደረግ እንቅስቃሴ ቡናማዎቹ ሲጫወቱ ድሬዎች ወደ ኃላ አፈግፍገው የመከላከል ቀጠናውን በሚገባ በመጠበቅ በቀጠለው ጨዋታ 20ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ሳሙኤል ዘሪሁን ሳጥን ውስጥ ሳይጠበቅ በቀኝ እግሩ በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ተክለማርያም እንደምንም ተፍቶ በድጋሚ ይዞበት ለድሬዎች የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራቸው ሆኖ አልፏል።
እየተቆራረጠ ቀዝቅዞ የቀጠለው ጨዋታ 32ኛው ደቂቃ ድሬዎች ከቀኝ መስመር ገብተው ዋለልኝ ገብሬ ለማሻገር የመታው ኳስ በቀጥታ ወደ ጎል አምርቶ ግብጠባቂው ተክለማርያም ወደ ውጭ ያወጣበት ሌላኛው የድሬዎች የጎል ሙከራ ነበር።
በሁለቱም በኩል በጥቂት የጎል ሙከራዎች የተመለከትንበት፣ ዓላማ የሌለው እንቅስቃሴ አብዝቶ ኳስን በማሸራሸር ብቻ ተገድቦ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየው ድሬዳዎች ከተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና በተሻለ መንቅሳቀስ መቻላቸው ካልሆነ በቀር ብዙም የጎል ሙከራዎች አልተመለከትንም። በ47ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን በፍጥነት ገብቶ መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳሱን የሚቀበል ተጫዋች ጠፍቶ በቀላላሉ የወጣው ኳስ እስከ ሰባኛው ደቂቃ ድረስ ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ጎል የቀረቡበት ብቸኛ አጋጣሚ ነበር።
በአንፃሩ ድሬዎች በአንድ አጋጣሚ በጥሩ የኳስ ቅብብል ወደ ፊት ሄደው አልያስ ማሞ በሁለት ተከላካዮች መሐል አሾልኮ ለአጥቂው ሪችሞንድ ኦዶንጎ አቀብሎት ኳሱ ጋር ቢደርስም ሚዛኑን ባለመጠበቁ ምክንያት እስኪዘጋጅ ድራስ ወንድሜነህ ደረጄ ደርሶ ተሸራቶ ያወጣበት ለድሬዎች ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር።
ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው አቡበከር ናስር በግራ መስመር ላይ ከሚፈጥረው ጫና ውጪ ሌሎቹ አጥቂዎች እና አማካዮች ወርደው በታዩበት የኢትዮጵያ ቡና እንቅስቃሴ 72ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከግራ መስመር ተከላካዮችን በእንቅስቃሴ አልፎ ወደ ሳጥኑ አጥብቦ በመግባት ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ሳምሶን አድኖበታል።
ድሬዎች ተጋጣሚያቸው ኳሱን አደራጅተው እና መስርተው እንዳይወጡ በማድረጋቸው ቡናዎች ረዣዝም ኳሶች በተደጋጋሚ በመጠቀም ሲጫወቱ ተመልክተናል። የቡናዎችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠሩ ረገድ ድሬዎች የተሳካላቸው ቢሆንም እንደወሰዱት ብልጫ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ለመፍጠር ዘግይተዋል። ምናልባትም በጨዋታው ሦስት ነጥብ በማግኘት አሸንፈው መውጣት የሚችሉበት ዕድል 77ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ወደ ፊት ጥሩ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች እንደሆነ የተመለከትነው
ባለ ተስዕጦ የግራ እግር የመስመር አጥቂ ሳሙኤል ዘሪሁን በሚገርም ሁኔታ ተከላካዮችን በማለፍ በግራ እግሩ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ መረብ ውስጥ ገባ ተብሎ ሲጠበቅ ለጥቂት በቋሚው ስር ታኮ የወጣው በድሬዎች በኩል የሚያስቆጭ ግልፅ የጎል አጋጣሚ ነበር።
80ኛው ደቂቃ የእጅ ውርወራን ጅማሬውን ያደረገው ኳስ ፍቅረየሱስ፣ ለአቡበከር፣ እንዳለ ደባልቄ መልሶ ሳጥን ውስጥ ለአቡበከር ሰጥቶት አጥቂው የግብጠባቂውን ሳምሶንን አቋቋም አይቶ የመታው እና ውጭ የወጣበት በኢትዮጵያ ቡና በኩል የመጨረሻ የጎል ሙከራ ነበር።
ወደ ጨዋታው መገባደጃ ላይ ኤልያስ ማሞ በግራ እግሩ ከሳጥን ውጭ በቮሊ የመታውን ግብጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ የተፋው አጥቂው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ሊደርስበት የነበረውን አጋጣሚ በድጋሚ ከወደቀበት ተነስቶ ኳሱን ያዘው እንጂ ለድሬዎች ሌላ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም በዚህ መልኩ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ለመጠናቀቅ ተገዷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ