የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-0 ኢትዮጵያ ቡና

በ5ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው የድሬዳዋ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በኃላ አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይና ካሣዬ አራጌ ተከታዩን አስተያየት ሰተዋል።

“የዛሬው ጨዋታ ሁለት መልክ ነበረው” ስምኦን ዓባይ (ድሬዳዋ ከተማ)

የጨዋታው እንቅስቃሴ

ከእረፍት በፊት እነርሱ የተሻሉ ነበሩ። ከእረፍት በኋላ ግን ኳሱን እና የእነርሱን እንቅስቃሴ ተቆጣጥረን መጫወት ችለናል። አጠቃላይ የዛሬው ጨዋታ ሁለት መልክ ነበረው። ከእረፍት በፊት እነርሱ ከእረፍት በኃላ እኛ.. ግን ውጤቱ ይሄ ሊሆን ችሏል። የእኔ ተጫዋቾች አልተረዱት ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያ ቡና በራሱ የሜዳ ክፍል ኳስ እንዲያሸራሽሩ ብቻ ነበር ለመፍቀድ ያሰብነው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እንደ ያሬድ ታደሰ ያሉ በልምዱ ብዙ ያልዳበሩ ወጣት ተጫዋቾች በታክቲካል ዲሲፒሊን ጠንካራ ተጫዋች እስኪሆኑ ድረስ ክፍተቶች ይፈጠራሉ። ከእረፍት መልስ ግን ክፍተታችን በሚገባ አርመን አሸንፈን መውጣት የምንችልበት ዕድል ፈጥረናል፤ ሳይሳካ ቀርቷል እንጂ።

“አንድ ቡድን መለካት ያለበት በማሸነፍ ብቻ መሆን የለበትም” ካሣዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለ ጨዋታው

ጥሩ ጨዋታ ነበር። ዛሬ ነጥብ ፈልገን አሸንፈን ለመውጣት የገባንበት ጨዋታ ነበር። በተለይ የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ነበርን። ያም ቢሆን የተጋጣሚ ቡድን የሰው ቁጥር አብዝቶ በስምንት ሰው ነበር ይከላከሉ የነበሩት። እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲኖሩ ደግሞ የመግቢያ ቦታዎች ጠባብ ነው የሚሆኑት። ቦታዎች በሰዎች ስለሚያዝ እንዲህ ሲሆን ምን ማድረግ እንዳለብን ማስተካከል አለብን እንጂ በዛሬው ጨዋታው ነጥብ ይዘን መውጣት ይገባን ነበር።

ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ አለመቻል

አንድን ነገር ተግባራዊ የምታደርገው በአንድ ሁለት ጨዋታ አይደለም፤ ጊዜ ይፈልጋል። አንድ ቡድን መለካት ያለበት በማሸነፍ ብቻ መሆን የለበትም። አንዱ መለኪያ ማሸነፍ ቢሆንም በተጋጣሚህ ቡድን ላይ የምትወስደው ብልጫ መታየት አለበት። ስለዚህ በንፅፅር ሲታይ ከተጋጣሚ የተሻልን ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ