የ2012 ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ተጀመረ

የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ሲጀመር ሻሸመኔ ከተማ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ልደታ ክ/ከተማ እና ፋሲል ከነማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም 8 ሰዓት የተጀመረው የቦሌ ክ/ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በተጋባዦቹ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ገና በጅማሮ ግብ ማስተናገድ የጀመረው ጨዋታው በ13 ደቂቃዎች ውስጥ ሶስት ጎሎችን አስመልክቷል። በሶስተኛው ደቂቃ የቅጣት ምት ያገኙት ፋሲሎች አጋጣሚውን በትዕግስት ዳልጋ አማካኝነት ወደ ጎል ቀይረው መምራት ጀምረዋል። ከፍተኛ የትኩረት ማነስ ችግር ሲታይባቸው የነበሩት ቦሌዎች ከሁለት ደቂቃ በኋላ ተጨማሪ ጎል በዲቦራ ጻውሎስ አማካኝነት ተቆጥሮባቸው አጀማመራቸው ተበላሽቷል። ገና በጊዜ የሚፈልጉትን ያገኙ የሚመስሉት ፋሲሎች መሪነታቸውን የሚያሰፉበት ሌላ ተጨማሪ ጎል በ13ኛው ደቂቃ በረድኤት ዳንኤል አማካኝነት አስቆጥረዋል።

ፋሲሎች ሦስተኛ ጎል ካስቆጠሩ በኋላ አጨዋወታቸውን ገድበው ተንቀሳቅሰዋል። በተቃራኒው ከተቻለ ሶስት ነጥብ ካልተቻለ ደግሞ አንድ ነጥብ ከጨዋታው ይዘው ለመውጣት ሲጥሩ የነበሩት ቦሌዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ለማድረግ ሞክረዋል። በተለይ ቡድኑ በህዳት ካሳ፣ ምስጋና ግርማ እና ቤቴልሄም ምንታሉ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ጥቃቶችን ሰንዝሯል።

በ35ኛው ደቂቃ በመስመር አጨዋወት ወደ ግብ ያመሩት ባለሜዳዎቹ በህዳት አማካኝነት ሙከራ ሰንዝረው መክኖባቸዋል። አሁንም ጥቃት መሰንዘራቸውን ያላቆሙት ቦሌዎች ከአምስት ደቂቃ በኋላ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ በግራ መስመር ቤቴልሄም በጥሩ የኳስ ቅብብል ወደ ሳጥን ያሻገረችውን ኳስ ህዳት ወደ ግብ መታው ግብ ጠባቂዋ አድናባታለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ የመጨረሻ እድል በረጅም ኳስ ያገኙት ቦሌዎች ኳስ እና መረብን አገኛኝተው የግቡን ልዩነት ለማጥበብ ቢሞክሩም የተቆጠረው ጎል ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮባቸው እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው ግማሽ ጅማሮ የኳስ ቁጥጥር የበላይ የሆኑት ቦሌዎች ጫናዎችን ማድረግ ቀጥለዋል። በተለይ ቤቴልሄም በተሰለፈችበት የግራ መስመር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥሯል። ጥረታቸው ሰምሮም በ61ኛው ደቂቃ የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ባንቺ መገርሳ አስቆጥራ የግቡን ልዩነት አጥባለች። ይህንን የፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረችው ባንቺ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ከርቀት አክርራ በመምታት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ሞክራለች። በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ እና በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ተጠናክረው የገቡት ቦሌዎች በ73ኛው ደቂቃ ህዳት ግብ ጠባቂዋን አልፋ ባመከነችው ኳስ እጅግ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ከዚህ ለግብ የቀረበ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ በ80ኛው ደቂቃ በሳምራዊት አስፋው አማካኝነት ለመሳት የሚከብድ ኳስ አምክኗል።

በጨዋታው መዳከሞች ሲስተዋልባቸው የነበሩት ፋሲሎች ለማጥቃት በወጡበት ሰዓት ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በ89ኛው ደቂቃ ቤቴልሄም ለአስቴር ደጋረገ አመቻችታ አቀብላት አስቴር አስቆጥራለች። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲሰነዘሩባቸው ለነበሩ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ቢጥሩም ተጨማሪ ግበብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ተጠናቋል።

ከቦሌ ክ/ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በመቀጠል የተደረገው የንፋስ ስልክ ክ/ከተማ እና ልደታ ክ/ከተማ ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል ልደታ ክ/ከተማ 2-1 አሸንፏል።

ብዙም የግብ ሙከራዎች ባልተስተናገዱበት ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ተቀራራቢ ብቃት በማሳየት ጨዋታቸውን አከናውነዋል። በ4ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ወደ ንፋስ ስልክ ያመሩት ልደታዎች በእየሩስ ወንድሙ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል።

በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ጨዋታቸውን እያከናወኑ የቀጠሉት ሁለቱ ቡድኖች እስከ 25ኛው ደቂቃ ድረስ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ተስኗቸው ታይቷል። በዚህ ደቂቃ የንፋስ ስልክ ተከላካዮች በረጅሙ ያላራቁትን ኳስ ትዕግስት ሽኩር አግኝታ ግብ ለማስቆጠር ጥራለች። ከሶስት ደቂቃ በኋላ በአንፃራዊነት በጨዋታው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት ልደታዎች የንፋስልክ የግብ ጠባቂ ሰርካለም ዓባይነህን ስህተት ተጠቅመው ግብ አስቆጥረዋል።

በኳስ ቁጥጥር ረገድ እየተሻሻሉ የመጡት ንፋስ ስልኮች በ40ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃ በረጅሙ የተላከን ኳስ ለማፅዳት የተዘናጉት የልደታ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት በቤቴልሄም ኪዳነማርያም አማካኝነት ግብ ተቆጥሮባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ግብ ያስተናገዱት ልደታዎች መልሰው መሪ ለመሆን በ47ኛው ደቂቃ ጥሩ እድል በፍሬህይወት በድሉ አማካኝነት ፈጥረው መክኖባቸዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ በ51ኛው ደቂቃ ጥሩ እድል አግኝቷል። ከመሃል ሜዳ በረጅሙ የተላከን ኳስ ተጠቅማ እየሩስ ግብ ለማስቆጠር ጥራ በጥሩ ሰዓት ኳሱም ለማፅዳት የወጣችው ግብ ጠባቂዋ አምክናባታለች። ፈጣን የመስመር ላይ አጥቂዎች የያዙት ንፋስ ስልኮች በ60ኛው ደቂቃ ሰላማዊት ተስፋዬ ከመሃል እንዲሁም በ71ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ ወደ ግብ ለመቀየር በሞከረችው ሙከራ ወደ ግብ ቀርበዋል። ጥሩ ጥሩ የኳስ ቅብብሎችን ሲፈፅም የነበረው ቡድኑ በጨዋታው መጨረሻ መዳከሞች ታይቶበት ግብ አስተናግዷል። ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው መስታወት አመሌ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ቡድናን አሸናፊ የሚያደርግ ግብ አስቆጥራለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ያለቀለት አጋጣሚ ያገኙት ንፋስ ስልኮች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረው መክኖባቸዋል።

ሌሎች የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች በተለያዩ ስታዲየሞች ተከናውነዋል። ገርጂ አካባቢ በሚገኘው የአካዳሚ ሜዳ የተደረገው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ለባለሜዳዎቹ ንግስት በቀለ ለተጋባዦቹ ደግሞ ዳሳሽ ሰውአገኝ ግብ አስቆጥረዋል። ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ጥሩነሽ አካዳሚን በዓለሚቱ ድሪባ ሐት-ትሪክ እንዲሁም በእናት ያደታ ሁለት ጎሎች ታግዞ 5-0 አሸንፏል። ለገጣፎ ለገዳዲ ደግሞ በሜዳው ቂርቆስ ክ/ከተማን ጋብዞ 1-0 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ