ስድስት ጎሎች ከተቆጠረበት የሰበታ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለብዙሃን መገናኛ አጋርተዋል።
“እኛ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ የሰራነውን ስህተት እነሱ መጨረሻ ላይ ደግመውልን አንድ ነጥብ ይዘን ወጥተናል።” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)
ጨዋታው እንዴት ነበር?
የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሚባለው ከእነ ጭማሪ ደቂቃው ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነገር ነበረን። ከእረፍት በኋላ ደግሞ እነሱ በብዙ ነገር የተሻሉ ነበሩ። ይህ ደግሞ የሆነው በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ አከታትለው ያስቆጠሩት ጎል በራስ መተማመናቸውን አሳድጎላቸው ነው። በእኛ በኩል የተከላካይ ክፍሌ የመዘናጋት ችግር አሳይቷል። በእንቅስቃሴ ደረጃም ቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ደቂቃዎች ወስደውብናል። ቢሆንም ግን እኛ የሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ የሰራነውን ስህተት እነሱ መጨረሻ ላይ ደግመውልን ነጥብ ይዘን ወተናል። በአጠቃላይ ግን ጠንካራ ቡድን ገጥመን ነጥብ መውሰዳችን ለእኛ ጥሩ ነው።
የቀድሞ ክለብህን በመግጠምክ ምን ተሰማህ?
የትም ብትሆን ለእግር ኳሱ ነው የምትሰራው። እኔ በፋሲል ቤት የሰራሁት ነገር አልፏል። ግን በእነሱ በኩል ከነበሩት የመጀመርያው 11 መካከል አስሩ ከእኔ ጋር የነበሩ ናቸው። እነሱንም መግጠም በመጠኑ ይከብዳል። ግን ከሞላ ጎደል እነሱም ለክለባቸው፤ እኔም ለክለቤ ስለሆነ የተጫወትነው ምንም ማለት አይደለም።
“ተጫዋቾቼ በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት እና ሶስት ደቂቃዎች ጨዋታውን ጨርሰናል በሚል በውስጣቸው በተፈጠረ ደስታ ስህተቶችን ሰርተናል።” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)
ስለ ጨዋታው
በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው እንቅስቃሴ የተመጣጠነ ቢመስልም እኔ እንደፈለኩት አላገኘሁትም። በዚህን በእረፍት ሰዓት ከተጨዋቾቼ ጋር በደንብ ተነጋግረን ነበረ። በሁለተኛው አጋማሽም ከነበርንበት ተላቀን የተሻለ ነገሮችን ለመፍጠር ሞክረናል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውም ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት 3-1 እየመራን ነበረ ነገር ግን ባለቀ ሰዓት ጎሎች ተቆጠሩብን። ይህ ጉዳይ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሃገራችንም ብሎም ለዓለማችንት ክለቦች ምህርት የሚሆን ነው። ጨዋታን ሙሉ በሙሉ ካልጨረስ እንቅስቃሴክ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ተጨዋቾቼ በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት እና ሶስት ደቂቃዎች ጨዋታውን ጨርሰናል በሚል በውስጣተቸው በተፈጠረ ደስታ ስህተቶችን ሰርተናል። ከግብ ጠባቂው ጀምሮ ትኩረታችንን አተን ነበረ። ቦታ አያያዛችን ልክ አልነበረም። በአጠቃላይ ቀድሜ እንዳልኩት ለዋንጫ ስለምንጫወት ከዚህ በኋላ የዛሬው ስህተታችን ትምህርት ይሆነናል። ተጨዋቾቼ ግን በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ባደረጉት እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ።
© ሶከር ኢትዮጵያ