ከፍተኛ ሊግ ሀ | ኤሌክትሪክ ነጥቡን ከመሪው ጋር ሲያስተካክል አክሱም፣ ገላን እና ኮምቦልቻ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ተከናውነው ኤሌክትሪክ፣ አክሱም፣ ገላን እና ወሎ ኮምቦልቻ ድል አስመዝግበዋል።

መቐለ ላይ ደደቢት ከ ሶሎዳ ዓድዋ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። ማራኪ እንቅስቃሴ እና በርካታ የግብ ሙከራዎች በታየበት ጨዋታ ግብ ለማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ሲሆኑ ግቧም በቃልኪዳን ዘላለም አማካኝነት የተገኘች ነበረች። የመስመር አማካዩ ፉሴይኒ ኑሁ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ጨርፎ ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው። አማካዩ ከግቡ በተጨማሪ ሌላም ከርቀት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው መጀመርያ ደቂቃዎች ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት የመረጡት ሶሎዳ ዓድዋዎች በአስራ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። በውድድር ዓመቱ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚገኘው ኃይልሽ ፀጋይ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በማስቆጠር ነው ቡድኑን አቻ ያደረገው። ሶሎዳ ዓድዋዎች ግቡ ከማስቆጠራቸው በፊትም በግብ አግቢው ሀይልሽ ፀጋይ ተመሳሳይ ወርቃማ ዕድል አምክነዋል።

በተመሳሳይ ጥሩ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሶሎዳ ዓድዋዎች ነበሩ ቀድመው ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉት። ኃይልሽ ፀጋይ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ጎል ቀይሮ ነው ቡድኑን መሪ ያደረገው። ዓድዋዎች በአጋማሹ በጋናዊው እድሪስ ዓብዱልናፊ እና ኃይልሽ ፀጋይ ሙከራዎች አድርገዋል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ደደቢቶች በሰባ ሶስተኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ዓብዱልበሲጥ ከማል ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ አስቆጥሮ ነበር ለቡድኑ ወሳኝ ግብ ያስቆጠረው። ሰማያዊዎቹ በመጨረሻው ደቂቃም በኃይሉ ገ/የሱስ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩበት ዕድል አግኝተው ተከላካዩ ኳሷን ወደ ግብነት መቀየር አልቻለም። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

መድን ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲን የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 በማሸነፍ ነጥቡን ከመሪው ጋር አስተካክሏል። በ7:00 በተደረገው በዚህ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ31ኛው ደቂቃ አዲስ ነጋሽ በፍፁም ቅጣት ባስቆጠረው ግብ በመምራት የመጀመሪያውን አጋማሽ ያጠናቀቀ ሲሆን የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ አደም አባስ ለኤክትሪክ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

አክሱም ላይ አክሱም ከተማ ከ ደሴ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአክሱም አሸናፊነት ተጠናቋል። ለአክሱሞች አዲስዓለም ደሳለኝ ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲያሳካ ረዳችውን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል።

ኮምቦልቻ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ ከ ፌዴራል ፖሊስ ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው አሸናፊነት ተጠናቋል። ለወሎ ኮምበልቻ እዮብ ወልደማርያም እና ቃለፍቅር መስፍን ግቦቹን ሲያስቆጥሩ ለፌዴራል ፖሊስ ቻላቸው ቤዛ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ከጨዋታው በኋላ የፌዴራል ፖሊስ አሰልጣኝ መሳይ በላይ ቅሬታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ብለዋል። “የነበረው ዳኝነት በጣም አሳፋሪ ነው። የተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ትክክል አይደለም። የእለቱ ዳኛ አቋቋሙ ትክክል አልነበረም። ከጀርባ ያልተነካ ኳስ ነው ፍፁም ቅጣት ምት የሰጠብን። የዳኞች ውሳኔ ውጤት የሚለውጥ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። ደጋፊው እንዲሁም ስለነበረው መስተንግዶ ግን በጣም እናመስግናለን።”

ወልዲያ ላይ ወልዲያ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃንን አስናግዶ ያለ ጎል አቻ ተለያይቷል።

ቅዳሜ ቢሾፍቱ ላይ ገላን ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በተጨማሪ ደቂቃ ብሩክ እንዳለ ያስቆጠራት ግብ ገላን ከተማን የዓመቱ የመጀመርያ ድልን እንዲያሳካ ረድታለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ