ከፍተኛ ሊግ ለ | ነቀምቴ ወደ መሪነት ሲሸጋገር መከላከያ፣ ጅማ፣ ቤንች ማጂ እና ካፋ ቡና የመጀመርያ ድላቸውን አሳክተዋል

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል። 

ነቀምቴ ላይ ነቀምቴ ከተማ ጋሞ ጨንቻን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ የደረጃ ሰንጠረዡን መምራት ጀምሯል። የነቀምቴን ብቸኛ የድል ኳስ ከመረብ ያገናኘው ቴዎድሮስ መንገሻ ነው።

መድን ሜዳ ላይ ኢኮሥኮ ከ መከላከያ ያደረጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በመከላከያ አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ከተስፋ ቡድን ያደገው መሐመድ አበራ ብቸኛዋን ግብ ሲያስቆጥር በ62ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ዘነበ ከበደ ከሜዳ በቀይ ካርድ የወጣባቸው ቢሆንም መሪነታቸውን አስጠብቀው መውጣት ችለዋል።

ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ከሀምበሪቾ ያደረጉትን ጨዋታ ባለሜዳው 1-0 አሸንፏል። ከጨዋታው በፊት የቦንጋ መምኅራን ትምህርት ኮሌጅ ለካፋ ቡና ሙሉ የትጥቅ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን የዞኑ ስፖርት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሽፈራው ገብረፃዲቅ ምስጋናቸውን ለኮሌጁ አስተላልፈዋል። ካፋ ቡና ጨዋታውን ያሸነፈበትን ብቸኛ ጎል በ36ኛው ደቂቃ በረከት ጌቱ አስቆጥሯል።

በሱሉልታው ያያ ቪሌጅ ሜዳ አዲስ አበባ ከተማ ከ ቤንች ማጂ ቡና ያደረጉትን ጨዋታ እንግዳው ቡድን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ለቤንች ማጂ ቡና ተዘራ ጌታቸው በ10ኛው ደቂቃ እንዲሁም የጨዋታው መገባደጃ ላይ ጌታሁን ገላዬ ግቦቹን ሲያስቆጥሩ አዲስ አበባን ከመሸነፍ ያላዳነች ጎል ጫላ ዲሪባ አስቆጥሯል።

ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከ ወለይታ ሶዶ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። ለሻሸመኔ ከተማ ሙሉቀን ተሾመ እና ከማል አቶም ሲያስቆጥሩ ለወላይታ ሶዶ ጥላሁን በቶ እና በረከት ወንድሙ አስቆጥረዋል። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል የታየ ሲሆን የሶከር ኢትዮጵያ ታማኝ ምንጮች ስለ ሁኔታው በሚከተለው መልኩ ገልፀውልናል፡-

ባለሜዳው 2-1 በሆነ ውጤት እየመራ ተጨማሪው ሦስት ደቂቃ አልቆ ባለበት ወቅት ሶዶዎች ጎል ያስቆጠሩ ሲሆን ወዲያው የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስረውን ፊሽካ ያሰሙት የዕለቱ ዳኛ በደጋፊው ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። የተወሰኑ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ልዩ ኃይልም በመምጣት ሁኔታውን ተቆጣጥሯል። ለተጋጣሚ ቡድን የሻሸመኔ የደጋፊ ማኅበሩ ያደረገው አቀባበል በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነበር። ”

ጅማ ላይ ጅማ አባ ቡና ሀላባ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላም የዓመቱ የመጀመርያ ድል አስመዝግቧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ