በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ከስድስቱ ጨዋታዎች አራቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ጌዴኦ ዲላ እና ኮልፌ ቀራኒዮ አሸንፈዋል።
ወደ ወራቤ ያቀናው ጌዴኦ ዲላ ባለሜዳው ስልጤ ወራቤን 2-1 አሸንፏል። ሁለቱ ቡድኖች ፈጣን እንቅስቃሴ በማሳየት ጨዋታውን ቢጀምሩም ቀስ በቀስ እየተቀዛቀሱ መጥተዋል። የወራቤው መሱፍ ያሲን ባደረገው አስደንጋጭ ሙከራ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ወራቤዎች የተሻሉ ነበር። በርካታ የኳስ ቅብብሎችን ለማድረግ ሙከራ ያሳዩት ወራቤዎች በተጋጣሚያቸው የሶስተኛ ሜዳ ሲደርሱ ሲቆረጥ የነበረ ሲሆን በ25ኛው ደቂቃ አማኑኤል ተፈራ እንዲሁም 39ኛው ደቂቃ ላይ ሮባ ዱካም ያደረጓት የግብ ሙከራዎች ለጎል የቀረቡ ነበሩ። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃም ከድር ታረቀኝ የግል ጥረቱን ተጠቅሙ ሳጥኑ ውስጥ ይዞት የገባው ኳስ በግቡ አናት የሰደደው ኳስ አስቆጪ የግብ እድል ነበር።
ዲላዎች በአንፃራዊነት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት በመምረጥ ወደራሳቸው የግብ ክልል አመዝነው የተጫወቱ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ከርቀት ዮሐንስ ኪሮስ እና ታምሩ ባልቻ ካደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በስተቀር የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ከእረፍት መልስ ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ወራቤዎች በ55ኛው አማኑኤል ተፈራ እንዲሁም በ63ኛው ደቂቃ ከድር ታረቀኝ ከርቀት ሞክረው ግብ ጠባቂው አድኖባቸዋል። በተቃራኒው በመልሱ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ዲላዎች ጥረታቸው ሰምሯል። በ69ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ዮሐንስ ኪሮስ ተቆጣጥሮ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ በግሩም አጨራረስ ዲላዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ወራቤዎች ከጎል ክልላቸው ነቅለው በመውጣታቸው በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን አጋጣሚ ታምሩ ባልቻ በሚገባ ወደፊት በመግፋት በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ዮሐንስ ኪሮስ አቀብሎት ዮሐንስ የዲላዎችን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላም ወራቤዎች ግብ ፍለጋ እጅጉን ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በ87ኛው ደቂቃ ላይም የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የዲላ ተጫዋቾች ፍፁም ቅጣት ምት የሰጡት የእለቱ ዳኛ ውሳኔን በመቃወም ለሁለት ደቂቃዎች ከዳኛው ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ የገቡ ሲሆን ፍፁም ቅጣት ምቱ ሊመታ ሲል የዲላው አምሳሉ መንገሻ የወራቤው ኩሴ ሞጨራን በክርኑ በመምታቱ ኩሴ መሬት በመውደቅ በምላሹ የአምሳሉን እግር ተማትቷል። ይህን ተከትሎም የእለቱ ዳኛ ለሁለቱም ተጫዋቾች ቀጥታ ቀይ ካርድ በማሳየት ከሜዳ ቢስወግዱም የዲላው አምሳሉ ከሜዳ ለመውጣት አንገራግሮ በቡድኑ ተጫዋቾች ተይዞ ከሜዳ ወጥቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ሮባ ዱካም ወደግብ በመለወጥ ልዩነቱን ወደ 2-1 አጥብቧል።
ውጥረት በታየበት የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ አማኑኤል የአቻነት ግብ የሚያስቆጥርበትን እድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በነዚህ ደቂቃዎች የዲላው አሰልጣኝ ደጋፊን ለሁከት በሚያነሳሳ መልኩ ግብ ጠባቂው እንዲወድቅ መልእክት ሲያስተላልፉ የታየ ሲሆን የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ከተሰማ በኋላ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ድንጋይ መወርወር የጀመሩ ቢሆንም ብዙም ሳይባባስ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውሏል። የፀጥታ ኃይሉ እንግዳው ቡድን በመሸኘትም ግዴታውን በአግባቡ ተወጥቷል።
በሌሎች ጨዋታዎች 07:00 ኦሜድላ ሜዳ ላይ አዲስ አዳጊው ኮልፌ ቀራኒዮ የዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው ኢትዮጽያ መድንን 2-0 ሲያሸንፍ ደሳለኝ ወርቁ በ45ኛው፣ ተመስገን ተስፋዬ በ76ኛው ደቂቃ የኮልፌን የድል ጎሎች አስቆጥረዋል።
አርሲ ነገሌ ላይ ነገሌ አርሲ ከ ባቱ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል። ቡታጅራ ከ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ፣ ከንባታ ሺንሺቾ ከ ደቡብ ፖሊስ እንዲሁም የካ ክፍለ ከተማ ከ ቂርቆስ ክ/ከተማ ያደረጓቸው ጨዋታዎች ደግሞ ያለ ጎል በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ