ሴቶች ፕሪምየር ሊግ| ባንክ ሲያሸንፍ አርባምንጭ እና ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመሩ ንግድ ባንክ ወደ ጊዜያዊ መሪነት የተሸጋገረበትን ድል አስመዝግቧል። አርባምንጭ እና ኤሌክትኪክ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

በፋሪስ ንጉሴ

አርባምንጭ ላይ የተደረገው የአርባምንጭ እና ኤሌትሪክ ጨዋታ 1 አቻ ተጠናቋል። ጨዋታው ከመጀመርያው ደቂቃ አንስቶ ማራኪ የቅብብል እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን 15 ደቂቃ ላይ ኤሌክትሪኮች በመሳይ ተመስገን አማካኝነት የሞከሩት ሙከራ ወደ ጎል በመቅረብ ቀዳሚ ሆነዋል። ኤሌክትሪኮች በአንድ ሁለት ቅብብል የአርባምንጭ ከተማን ተከላካዮች አታለው በድጋሚ በመሳይ ተመስገን አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን 28ኛ ደቂቃ ላይም በአርባምንጭ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ጥፋት ተሰርቶባት የፍፁም ቅጣት ምት አስገኝታለች። ፍጹም ቅጣት ምቱንም ሰሚራ ከማል በአግባቡ ተጠቅማ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥራለች።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አርባምንጭች 35 ደቂቃ ላይ ርብቃ ጣሰው ከርቀት መታ ባስቆጠረችው ጎል አቻ መሆን ችለዋል። 39ኛ ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኳ ትመር ጠንክር ከርቀት አክርራ መታ በግብ ጠባቂዋ የተመለሰባት የመጀመርያ አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረውና የማሸነፍ ፍላጎት በሁለቱም ክለቦች በኩል የታየበት ሲሆን ሁለቱም ክለቦች የማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሞክሩም ታይተዋል። አርባምንጭ ከተማዎች በረጅሙ የሚጥሏቸው ኳሷች አመዛኞቹ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሲሆን 55ኛው ደቂቃ ላይም በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሰርካለም ባሳ ጥሩ የማግባት ዕድል አጊኝታ ሳትጠቀም ቀርታለች።

በኤሌክትሪክ በኩል 74ኛ ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል እንግዳዎቹ የአርባምንጭ ተካላካዮችን በማታለል በምንትዋብ ዮሐንስ አማካኝነት ያለቀለት የማግባት እድል አግኝተው አገባች ተብሎ ሲጠበቅ ጥሩ ቀን ባሳለፈቸረው ግብ ጠባቂዋ ተመልሶባታል። በሁለቱም በኩል ጥሩ የማሸነፍ ስሜት የታየበት ጨዋታም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሲኤምሲ በሚገኘው ባንክ ሜዳ ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-1 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 7 አሳድጓል። የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል በተጠናቀቀበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ረሒማ ዘርጋው ንግድ ባንክን ቀዳሚ ስታደርግ እድላዊት ተመስገን በ76ኛው ደቂቃ እንግዶቹን አቻ አድርጋለች። ሆኖም ብዙ ሳይቆይ ዓለምነሽ ገረመው የንግድ ባንክን አሸናፊነት ያረጋገጠች ጎል ማስቆጠር ችላለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ